ማዕከላቱ ለጤናማ ግብይት ምን ያህል እያገዙ ነው?

You are currently viewing ማዕከላቱ ለጤናማ ግብይት ምን ያህል እያገዙ ነው?

የላፍቶ ቁጥር ሁለትን ጨምሮ እስካሁን በተገነቡት ማዕከላት 1037 ሱቆችና ግዙፍ መጋዘኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው

ግዙፍ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላትን ገንብቶ ለአገልግሎት የማብቃቱ ተግባር ቀጥሏል። ከሰሞኑ (ሰኔ 03 ቀን 2017 ዓ.ም.) ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የላፍቶ ቁጥር ሁለት ሁለገብ የገበያ ማዕከል ተጠቃሽ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ሁሌም ሕዝባችንን አዳምጠን ተጨባጭ ምላሽ እንሰጣለን፡፡ አዳምጠን ከንፈር መጥጠን አንመለስም፡፡ አስመስለን አንናገርም፡፡ ለሕዝባችን በታማኝነት፣ በቅንነት፣ በትጋት በመሥራት የኑሮ ጫናን የሚያቃልል ተግባር እያከናወንን ነው” ብለዋል፡፡

“እስካሁን ካከናወናቸው በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ካላቸው ፕሮጀክቶች መካከል የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ንረትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከቱ የሚገኙ በከተማችን አምስቱም በሮች ማለትም በላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ለሚ ኩራ እና  ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ተጠቃሾች ናቸው” ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ እነዚህን የገበያ ማዕከላት በመገንባታቸውና ዘመናዊ የአሠራር ስርዓት በመዘርጋቱ በርካታ ዉጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል። በተለይም፤ ከዚህ ቀደም በአምራች እና በሸማቹ መካከል ጋሬጣ ሆኖ የነበረውን የደላላ ሰንሰለትን መቆራረጥ በመቻሉ እና በውድድር ላይ የተመሰረተ የግብይት ስርዓት በመፈጠሩ ሸማቹ ማህበረሰብ እፎይታ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

 እንደ ከንቲባዋ ገለፃ፤ ከተማ አስተዳደሩ ለግንባታው ያወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመመለስ ሳይሆን፤ ለፅዳት ከሚወጣ ወጪ ውጪ አገልግሎቱን በነጻ በማቅረብ ምርት በስፋት የሚቀርብበት ሁኔታ እንዲፈጠር በትኩረት እየሠራ ይገኛል። የንግድ ትስስርን ለማሳለጥ፣ የግብይት ስርዓቱን ጤናማ ለማድረግ መንግስት ሚናውን ይወጣል፡፡ አዲስ አበባ ላይ እየተሠራ ያለው ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ አምራቾች ምርት ማከማቻና መሸጫ ቦታ ሳይቸገሩ የሚሸጡበት ሁኔታ መፍጠር ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያለው የከተማው ነዋሪ የሚደርስበትን የኑሮ ጫና ለማቃለል ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡ ይህ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይጨምራል፡፡ የህዝብን እና የመንግስትን ግንኙነት ያሳድጋል፡፡ ወደፊትም ከተማ አስተዳደሩ ለሕዝቡ የገባቸውን ቃሎች በተግባር እየፈፀመ ይሄዳል፡፡

የላፍቶ ቁጥር ሁለት የገበያ ማዕከል ከ8 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት በላይ ያረፈ ነው። ማዕከሉ ሁለት ዘመናዊ ምርት ማቆያ መጋዘኖች፣ 9 የጅምላ ማከፋፈያዎች (ሞሎች) እና 159 ሱቆች አሉት፡፡ የላፍቶ ቁጥር ሁለት የገበያ ማዕከልን ጨምሮ እስካሁን በተገነቡት  ማዕከላት ውስጥ 1037 ሱቆችና ግዙፍ መጋዘኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አሳውቀዋል፡፡

ለመሆኑ ቀደም ሲል የተመረቁ ማዕከላት ከታለመላቸው አላማ አንጻር እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ በተመለከተ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ቅኝት አድርጓል፤ የሚመለከታቸውን አካላትም አነጋግሯል፡፡

ከሩቅ ለማንም ጎልቶ ይታያል። እየቀረቡት ሲሄዱ ግዝፈቱ ይጨምራል። ቅጥረ ግቢው ሠፊ ነው። ፈረስ ያስጋልባል። እግረኞችን እና አሽከርካሪዎችን በአግባቡ ማስተናገድ የሚችሉ ሰፋፊ መንገዶች ተነጥፈዋል። የጣራቸው ቅርፅ ግማሽ ጨረቃ የሆኑ ትላልቅ ሕንፃዎች በተንጣለለው ግቢ ውስጥ ቆመዋል፡፡ እያንዳንዱ ሕንፃ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ሱቆች አሉት፡፡ ሱቆቹ፤ ከአምራቾች ቀጥታ በቀረቡ የግብርና ምርቶች (በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሰብል፣ በእንስሳት ተዋፅኦ…) እንዲሁም በኢንዱስትሪ ምርቶች (ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ዘይት…) ተሞልተዋል። የነጋዴ እና የሸማች መስተጋብር፣ የጫኝና አውራጅ የሥራ እንቅስቃሴ… የግዙፉን ማዕከል ዓላማ ሕይወት ሰጥተውታል፡፡ በቦታው ተገኝተን፣ ከግቢ እስከ ውስጥ ተዟዙረን፣ በዓይናችን ተመልክተን ከሞላ ጎደል በዚህ መልክ ገፅታውን ለማቅረብ የሞከርነው፤ የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከል ነው፡፡ 

ወይዘሮ ብዙነሽ ነጋሽ፤ በማዕከሉ የግብርና ምርቶችን ለመግዛት ከመጡ በርካታ ሸማቾች አንዷ ናቸው፡፡ መኖሪያቸውን በጣፎ ኮንዶምኒየም ያደረጉት ወይዘሮዋ፤ ወደ ማዕከሉ መምጣት ከጀመሩ ዓመት እንዳለፋቸው በማስታወስ፤ በዕለቱ የመጡበትን ምክንያት እና ስለፈፀሙት ግዢ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡ “ዛሬ ጤፍ ገዝቻለሁ፡፡ በኪሎ 130 ብር ነው የገዛሁት፡፡ ሌሎች ነጋዴዎች ጋር ጠይቄ ነው ወደማዕከሉ የመጣሁት፡፡ ከዚህ ያነሰ ጥራት ያለው ጤፍ በኪሎ 145 ብር ነው። እዚህ ያሉት ነጋዴዎች ጤፋቸው በጣም ምርጥ ነው፡፡ ጥራቱም ዋጋውም ከሌሎች ነጋዴዎች በጣም የተሻለ ነው። ድንችም፣ ሽንኩርትም ገዝቻለሁ፡፡ የወር አስቤዛዬን በአብዛኛው ከዚህ ነው የምገዛው። ለልጆቼ ወተት፣ አቮካዶ፣ ሙዝና ብርቱካንም ከዚህ ውጪ አልገዛም፡፡ እዚህ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ይገኛል፡፡ ሁሌም አዳዲስ ምርት ይገባል፡፡ ዋጋውም የተተመነ ስለሆነ ያለክርክር የምፈልገውን አማርጬ ነው፤ የምገዛው፡፡”

በባለ ሁለት ሊትር ፕላስቲክ ኮዳ ትኩስ የላም ወተት አስቀድተው፣ አንድ ኪሎ አይብ እንዲሁም ግማሽ ኪሎ ቅቤ አስመዝነው በሞባይል ስልካቸው አማካኝነት ሂሳብ ሲከፍሉ ያገኘናቸው አቶ ዳንኤል መሐሪ በበኩላቸው፤ “የግብይት ማዕከሉ ለአገልግሎት ከበቃበት ጊዜ ጀምሮ፤ ቋሚ ደንበኛ

ሆኛለሁ። ቢያንስ በሳምንት ሁለት ቀን እመጣለሁ። አሁን ላይ ለህመም ከሚዳርጉን ነገሮች አንዱ ከምግብ ጋር የተያያዘ ነው። እኔ ጤናዬን ለመጠበቅ ስፖርት መሥራትንና አመጋገቤን ማስተካከል ላይ አተኩራለሁ። እዚህ ማዕከል የሚሸጠው ወተት፣ አይብ፣ ቅቤ፣ አትክልትና ፍራፍሬ… ትኩስ እና ጥራቱ የተጠበቀ ነው፡፡” በማለት የማዕከሉ ቋሚ ተጠቃሚ የሆኑበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡ የማዕከሉ ፅዳት፣ የዋጋ ተመጣጣኝነት፣ የባለሙያዎች ያልተቋረጠ ክትትልና ቁጥጥር፣ ለትራንስፖርት ያለው ምቹነት፣ የፓርኪንግ አገልግሎት መኖር ከሌሎች መሰል አገልግሎት መስጫዎች በእጅጉ የተሻለ መሆኑንም መስክረዋል፡፡

በማዕከሉ ምርታቸውን ለሸማቾች እያቀረቡ ካሉ ነጋዴዎች አንዱ ናቸው፤ አቶ አብርሀም ንጉሴ። በማዕከሉ ውስጥ በተሰጣቸው የምርት ማከማቻ እና መሸጫ ዘመናዊ ሱቅ ከሌሎች አጋዥ ሠራተኞቻቸው ጋር በመሆን ምርቶችን ሲያስገቡ፣ በዓይነት በዓይነቱ ሲደረድሩ፣ ሲሸጡ አግኝተን በሞቀ ገበያቸው መሃል ገብተን፤ እየሰጡ ስላለው አገልግሎት፣ ስለምርት አቅርቦት፣ ስለሸማቹ ተጠቃሚነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ለጥቂት ደቂቃዎች ያክል አነጋግረናቸዋል። እሳቸው በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት ከሆነ፤ ወደ ማዕከሉ ከገቡ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን በብዛትና በዓይነት ለሸማቹ ያቀርባሉ፡፡ ለገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች ውስጥ 70 ከመቶ ያክሉ በራሳቸው የእርሻ መሬት የሚመረቱ ሲሆን፤ ቀሪውን ከሌሎች አምራቾች ይገዛሉ፡፡

ከእሁድ እስከ እሁድ ትኩስ እና ጥራታቸው የተጠበቀ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን የሚያቀርቡት አቶ አብርሀም፤ ምርት የሚያቀርቡበትን ሁኔታ እንደሚከተለው አብራርተዋል፤ “በርካታ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን በኦሮሚያ ክልል ቆቃ እና አፋር ክልል ዱፍቲ ካሉኝ የእርሻ መሬቶች አስገባለሁ። ሽንኩርት በሳምንት ሦስት ጊዜ፣ ቲማቲም ሁለት ጊዜ፣ ድንች ሁለት ጊዜ፣ አቮካዶ እና ማንጎ አንድ ጊዜ አስገባለሁ፡፡ የማስገባቸው ምርቶች ጥራታቸው በጣም የተሻለ ነው፡፡ ዋጋውም ተመጣጣኝ ነው፡፡ እኛ ጋ የሚሸጠው ምርት ከውጭ ነጋዴዎች ጋር ሲወዳደር ዋጋው ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ሽንኩርት ውጪ 80 ብር ሲሸጥ፤ እኛ ጋ 60 እና 65 ብር ነው። ቲማቲም እና ድንች ከ20 ብር ጀምሮ ይሸጣል፡፡ ጥቅል ጎመን ከ25 ብር ጀምሮ እዚህ አለ፡፡ ካሮት በውጪ ያሉ ነጋዴዎች በኪሎ እስከ 75 ብር ሲሸጡ፤ እኛ ጋ 40 እና 45 ብር ነው፡፡ በማዕከሉ ያሉት ሌሎች ነጋዴዎችም የሚያቀርቧቸው ምርቶች ጥራት ያላቸውና በዋጋቸውም ዝቅተኛ ናቸው፡፡”

“ይህ ማዕከል ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ለነጋዴውም ሆነ ለሸማቹ ትልቅ እፎይታን ፈጥሯል፡፡ እዚህ ማዕከል ከመግባታችን በፊት የደላላ መጫወቻ ነበርን፡፡ በደላሎች ፈርቅ (ፍትሐዊ ያልሆነ ጭማሪ) ይያዝብናል፤ ይወሰድብናል። ምቹ እና ቋሚ የሆነ የመሸጫ ቦታም ስንቸገር ቆይተናል። አሁን ላይ በመንግስት ይህ ችግር ተቀርፏል፡፡ በጣም ዘመናዊ በሆነ ሰፊ ሱቅ ምርታችንን ለተጠቃሚው በቀጥታ ማቅረብ ችለናል። ቦታው ሽታ የለውም፣ ቆሻሻ የለውም፡፡ ንጹህና ምቹ በሆነ የገበያ ሥፍራ ከሸማቹ ጋር በቀጥታ እንገናኛለን፡፡ ሥራችንም ውጤታማነቱ እያደገ መጥቷል፡፡” የሚሉት አቶ አብርሀም፤ በእርሻ መሬት ለ12፣ በሱቅ ለ5 በድምሩ ለ17 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።

በእንስሳት ሃብቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ፤ ለዜጎቿ የሥጋ እና የወተት ምርቶችን በጥራት እና በብዛት ማቅረብ ላይ ችግር እንዳለባት ይነገራል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ጉድለቶች ምርቱን ሰብስቦ ለተጠቃሚው ለማድረስ የሚያስችል ዘመናዊ የአሠራር ስርዓት አለመዘርጋቱ አንዱ ነው፡፡  በአዲስ አበባ መግቢያ በሮች ላይ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የግብርና ምርት መሸጫ እና ማከማቻ ማዕከላት ይህንን ክፍተት በመሙላት እረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ እና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኙ የእንሰሳት እና የእንሰሳት ተዋፅኦ ምርት አምራቾችና አቅራቢዎች ደረጃውን የጠበቀ ምርት በዓይነት እና በብዛት የሚያቀርቡበትን ሁኔታ በየማዕከላቱ ለተመለከተ እነዚህን መሰል ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ባለማሟላት ያለፉ ጊዜያት ያስቆጫሉ፡፡ በለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከል ቁጥራቸው የበዛ የእንሰሳት ተዋጽኦ ምርቶችን የሚያቀርቡ አምራች ነጋዴዎችም በሥራ ላይ ይገኛሉ።

“ፍሬሽ ፋርምስ” በማዕከሉ ውስጥ የእንሰሳት ተዋፅኦ ምርቶቻቸውን ከሚያቀርቡ መሰል አቅራቢዎች አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ ለምግብነት የተሰናዳ ጥራት ያለው የዶሮ ስጋ፣ የዓሣ ስጋ፣ ወተት፣ ቅቤ፣ ቺዝ (አይብ) ያቀርባል። ሰፊ በሆነው የምርት ማከማቻ እና መሸጫ ሱቅ ውስጥ ሁለት ወጣቶች  በቅልጥፍናና በትጋት ምርቶችን ከተለያዩ ግዙፍ ማቀዝቀዣዎች (ፍሪጆች) እያወጡ ለደንበኞች ይሸጣሉ፡፡ በዚህ መካከልም አዳዲስ የዶሮ ሥጋ፣ አይብ፣ ቅቤ የመሳሰሉ ምርቶች ሲገቡ ተመልክተናል። ስለ ሥራ እንቅስቃሴው አስመልክቶ ሃሳቡን ያካፈለን ከሁለቱ ትጉህ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት ዳዊት ሞገስ ነው። እንደ ወጣቱ ገለጻ፤ ወደማዕከሉ ከገቡ ከዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ሥራ ከጀመሩ ጀምሮ ምርታቸውን ያለማቋረጥ በየዕለቱ ለሸማቹ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ምርታቸውን ካራ አካባቢ ካለው የእንሰሳት እርባታ እና የእንሰሳት ተዋፅኦ ማቀነባበሪያ ድርጅት በቀጥታ ያቀርባሉ፡፡

ማዕከሉ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ፤ ለትራንስፖርት አመቺ በሆነ ሥፍራ፣ እጅግ ዘመናዊና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ፤ ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማቅረብ እንዳስቻላቸው የሚገልፀው ወጣት ዳዊት፤ እኛ ባነጋገርንበት ወቅት (ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም.) ምርታቸውን በምን ያክል ዋጋ እያቀረቡ እንደሆነ ሲያስረዳ፤ “ቅቤ በኪሎ 800 ብር፣ ቺዝ በኪሎ 750 ብር፣ ሙሉ የፈረንጅ ዶሮ ሥጋ 450 ብር፣ ዓሣ በኪሎ 400 ብር እናቀርባለን። እነዚህን ምርቶቻችንን በተመሳሳይ ለትላልቅ ሆቴሎችም እናቀርባለን። እዚህ ማዕከል የምንሸጠውን ምርት ለሆቴሎች በዋጋ ከፍ አድርገን ነው የምንሸጠው፡፡ ለምሳሌ ቅቤ በኪሎ 950 ብር፣ ቺዝ በኪሎ 900 ብር፣ ሙሉ የዶሮ ሥጋ በ550 ብር ነው ለሆቴሎች የምናቀርበው” በማለት የገበያውን ሁኔታ ገልፆልናል፡፡ በማዕከሉ ቋሚ እና ምቹ የግብይት ቦታ ማግኘታቸው ተጨማሪ ደንበኞችን ማፍራት እንዳስቻላቸው እና ተጠቃሚነታቸውንም ከፍ እንዳደረገውም አያይዞ ነግሮናል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ ስምንት የሚገኘው የአቃቂ ቃሊቲ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከል ልክ እንደ ለሚ ኩራ የግብርና ምርት መሸጫ እና ማከማቻ ማዕከል ሁሉ ለከተማው ነዋሪ እና ለንግዱ ማህበረሰብ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ አቶ ማሞ ዶሌ፤ በዚህ ማዕከል ውስጥ መሥራት ከጀመሩ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ጥራጥሬ፣ በርበሬ እና የቅመማ ቅመም ምርቶችን ያቀርባሉ፡፡ በአላባ ካላቸው የእርሻ መሬት የሚያመርቱትን በርበሬ፣ ቅመማ ቅመም ቀጥታ በመጫን ነው ለሸማቹ የሚያቀርቡት፡፡ ምርቱ ጥራት ያለው እና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥ ስለሆነ፤ ሸማቹ በብዛት ይገዛል፡፡

የግብርና ምርት መሸጫ እና ማከማቻ ማዕከላት የታለመላቸውን ዓላማ ከግብ እንዲያደርሱ የአምራች ነጋዴዎች ሚና የላቀ ነው፡፡ ለሸማቹ ማኅበረሰብ፤ በተለይም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ጥራቱን የጠበቀ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ዓላማን ለማሳካት እንደ አቶ ማሞ ዓይነት ትጉህ ሠዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እሳቸው ሱቃቸው ምርት እንዳይጎለው፣ ደንበኞቻቸው ለመሸመት መጥተው የፈለጉትን ሳያገኙ እንዳይመለሱ፣ የበርበሬ፣ የቅመማ ቅመም፣ የሰብል እና መሰል የግብርና ምርቶችን በብዛት እና በጥራት ያቀርባሉ። የአቅርቦታቸውን ሁኔታ ሲያብራሩ፤ “በርበሬ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይገባል። ቅመማ ቅመም እና ጥራጥሬ በሁለት ሳምንት አንዴ ይገባል። ጥራቱን የጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ስለማቀርብ ሸማቹ በደስታ ነው የሚገዛው፡፡ በማዕከሉ አቅራቢያ በርካታ የበርበሬ እና የቅመማ ቅመም ሱቆች አሉ፡፡ በደንበኛ ብዛት ግን እኛጋ የተሻለ ነው፡፡ በማዕከሉ ወፍጮ ቤት አለ፡፡ የምናቀርበው በርበሬ ደረቅ ስለሆነ፤ እዚያው ገዝተው እና ቅመማ ቅመም ተጠቅመው አስፈጭተው የሚሄዱበት ሁኔታም ተመቻችቷል፡፡” ብለዋል፡፡

ሁሉ ነገር ተሟልቶለት ለአገልግሎት በበቃው የግብይት ማዕከል ውስጥ በዝቅተኛ የኪራይ ዋጋ የሚሠሩበት ዕድል መፈጠሩ፤ ሥራቸውን በትጋት እና በአገልጋይነት መንፈስ ለመወጣት አቅም እንደፈጠረላቸው አቶ ማሞ ይናገራሉ። ይህ ሥራቸው፣ በሸማች ማዕከሉ ተቆጣጣሪ እና አመራር አካል ፊት ተመዝነው ምስጉንነታቸው በመረጋገጡ፤ በከተማ አስተዳደር ደረጃ በተዘጋጀ የምስጋናና የማበረታቻ መርሃ ግብር ላይ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ እጅ የምስክር ወረቀት መቀበላቸውን ያነሳሉ። በከተማ አስተዳደር ደረጃ በሥራቸው የተሰጣቸው ዕውቅና ለቀጣይ የተሻለ ሥራ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል። በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ መንግስት ማዕከሉን ከመገንባት ጀምሮ፣ መሰረተ ልማቱ የተሟላለት የምርት ማከማቻ እና መሸጫ ሱቅ፣ በዝቅተኛ የኪራይ ክፍያ ተጠቃሚ ስላደረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ማዕከሉ ከዋና መንገዱ የተወሰነ ርቀት ገባ ብሎ መገንባቱ በሸማቾች ዘንድ የነበረውን ያለመታወቅ ክፍተት በዓላትን መሰረት በማድረግ በገበያ ማዕከሉ በሚሰናዱ ባዛሮች፣ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በማስተዋወቅ ሸማቹ እና ነጋዴው የሚገናኙበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ማዕከሉ የሚመጣው የሕብረተሰብ ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ስለሚያገኙ ሸማቾች ከከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ይመጣሉ፡፡

የግብርና ምርት መሸጫ እና ማከማቻ ማዕከላቱ የንግድ ሥርዓቱን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ የማድረግ አዲስ አሠራርን ያስተዋወቁ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የተመደቡ የማዕከላቱ አመራሮች ያረጋግጣሉ፡፡ አቶ ዮሚዩ መርጋ በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የግብይት ባለሙያ ሲሆኑ፤ የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከልን የማስተባበር ኃላፊነት በተወካይነት እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ ማዕከሉ ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ያስችላሉ ብሎ ካቋቋማቸው የግብርና ምርት መሸጫ እና ማከማቻዎች አንዱ ነው፡፡  እንደሌሎቹ ማዕከላት ሁሉ በዚህ ማዕከል ጥራት ያላቸው የተለያዩ የግብርና፣ የእንስሳት ተዋፅኦ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በብዛት ይቀርባሉ፡፡ ምርቶቹ በሌሎች ነጋዴዎች ከሚሸጡበት ዋጋ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ ይደረግባቸዋል፡፡ የምርቶቹ የመሸጫ ዋጋ በጥራት ደረጃቸው ተለይቶ በየሳምንቱ በንግድ ቢሮ ይፋ በሚሆን መረጃ መሰረት የሚከናወን ነው፡፡

እንደ አቶ ዮሚዩ ገለጻ ፤ በለሚ ኩራ የግብርና ምርት መሸጫ እና ማከማቻ ማዕከል ውስጥ 15 የጅምላ፣ 34 የችርቻሮ፣ 31 የሰብል እና ጥራጥሬ ሱቆች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ምርታቸውን ለማከማቻ የተዘጋጁ ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዘኖችም በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፡፡ በማዕከሉ የአቅርቦት እጥረት የለም፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ድረስ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የመሰረተ ልማቱን ጥራትና ፅዳት የመከታተል፣ ምርቶች በጥራት እና በበቂ ሁኔታ መግባታቸውን የመከታተል፣ ዋጋ የመተመን፣ በተተመነው ዋጋ እየተሸጡ ስለመሆናቸው የመከታተል ኃላፊነትን ይወጣል፡፡ እኛም በዚህ ማዕከል ይህንኑ ኃላፊነት እየተወጣን እንገኛለን፡፡ በዚህ አገልግሎት ነጋዴውም ሸማቹም በጣም ደስተኛ ናቸው፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከል ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ብሩክታይት መብራቱ፤ ማዕከሉ እየሰጠ ስላለው አገልግሎት አብራርተዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ ማዕከሉ አንድ መጋዘን፣ 72 ሱቆች እና ወፍጮ ቤት አሉት፡፡ ማዕከሉ መሰረተ ልማት የተሟላለት እና ዘመናዊ ነው፡፡ በማዕከሉ ሰብል፣ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ የእንሰሳት ተዋፅኦ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በዋናነት ግብይት ይከናወንበታል፡፡ ይህ አገልግሎት በአምራቹ እና በሸማቹ መካከል የሚገባውን ደላላ እና የሚፈጠረውን የኑሮ ውድነት የሚያስቀር ነው፡፡ ሸማቹ ወደ ማዕከሉ መጥቶ ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገዛ ባዛሮችን እና ሌሎች የማስታወቂያ እንዲሁም ግንዛቤ የመፍጠሪያ ስልቶችን እንጠቀማለን፡፡ በማዕከሉ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራት ከፍተኛ ስለመሆኑ ሸማቹ ሕብረተሰብ በስፋት የሚመሰክርላቸው ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም በጥራት እና በዋጋ ላይ ያልተቋረጠ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡

 “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሸማቹን እና አምራቹን ቀጥታ ለማገናኘት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡  በከተማዋ አምስቱም የመውጫ እና መግቢያ በሮች ላይ የገነባቸው እና እየገነባቸው ያሉ የግብርና ምርቶች መሸጫ ገበያ ማዕከላት ከሥራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡” ያሉት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ፤ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በመመደብ ያስገነባቸውን እና ለአገልግሎት ያበቃቸውን የግብርና ምርቶች መሸጫ ገበያ ማዕከላት የክልል አምራቾች ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ምርታቸውን በማቅረብ እና በመሸጥ የከተማው ነዋሪ ማሕበረሰብ ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግን ዓላማ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ማዕከላቱ የተገነቡባት አዲስ አበባ፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ከተማ ወይም መዲና መሆኗን በተግባር ለማረጋገጥ እንደ አንድ ምሳሌ ተደርገው የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ኃላፊዋ አያይዘው እንዳስረዱት፤ አምራቾች ሦስት መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህም፡- በማዕከሉ ገብተው ምርታቸውን የሚያቀርቡ እና የሚሸጡ አምራቾች የሚያቀርቡትን ምርት በመደበኛው ገበያ ከሚሸጠው ተመሳሳይ ምርት ዋጋ ከ15 እስከ 20 ከመቶ ቅናሽ አድርገው ለመሸጥ መስማማት፣ ምርታቸውን በማዕከሉ በሚገኙ ሱቆች ለማቅረብ የሚመጡ አምራቾች የራሳቸው የሆነ የእርሻ ማሣ ያላቸው ስለመሆኑ ሕጋዊ ሰነድ ማያያዝ እንዲሁም ምርታቸውን ያለማቋረጥ ዓመቱን ሙሉ ማቅረብ መቻል የሚሉት ናቸው፡፡

የማዕከላቱ ፋይዳ በምሁራን እይታ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተገንብተው ለአገልግሎት እየበቁ ያሉ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላት በህብረተሰቡ ላይ ያለውን የኑሮ ጫና በመቅረፍ እረገድ ያላቸውን ሚና በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡን የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር አቶ ፋሲል ተዘራ፤ “የኑሮ ውድነቱን እያባባሱት ካሉ ነገሮች መካከል አንዱና ዋናው  በሸማቹና  በአምራቹ መካከል  የሚኖር  ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ነው:: በተለይ ጣልቃ ገብነቱ በመሰረታዊ ፍጆታዎች ይበልጥም በግብርና ምርቶች ላይ ሲሆን ችግሩ ይበረታል:: በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ የገበያ ማእከላት  የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በዓይነት፣ በብዛት፣ በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ያግዛሉ፡፡ ሸማቹም እነዚህን ምርቶች በአቅራቢያው በመግዛት ይጠቀማል፡፡ ከማዕከላቱ ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ከማግኘት በተጨማሪ፣ ሁሉንም ዓይነት ምርቶች በአንድ ማዕከል ለመግዛት የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ ለትራንስፖርት የሚወጣውን ወጪ፣ በተለያየ አካባቢ ለግዢ በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚባክነውን ጊዜ ይቀንሳል፡፡” ብለዋል፡፡

አያይዘውም፤ ከፍተኛ መዋዕለነዋይ ፈሰስ የተደረገባቸውን ግዙፍ እና ዘመናዊ ማእከላት ለአገልግሎት ከማብቃት ባለፈ፤ ምን ያህል ህብረተሰቡን እየጠቀሙ ነው? ምንስ ችግር  አለባቸው? እንዴትስ ይደገፉ? የሚለውን በጥናት መለየት እና ተከታታይነት ያለው ድጋፍና ክትትል እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ መንግሰት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ ያለውን የበጋ መስኖ ልማት እና የከተማ ግብርና ዓይነት ሥራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ምክረ-ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review