የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራን ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
የውይይት መድረኩ ምሁራን በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚኖራቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ለሂደቱ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ-ሀሳቦችን ለማሰባሰብ መዘጋጀቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ጥቂቶች የሚሳተፉበት ሂደት ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ባለቤት የሚሆንበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አክለውም ምሁራን ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም ጥናት እና ምርምሮችን እያከናወኑ ሂደቱን ማገዝ እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሀሳብ ያቀረቡት ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ምሁራን በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ተሳትፎ የማድረጋቸውን አስፈላጊነት በተለያዩ ሳይንሳዊ አመክንዮዎች አስረድተዋል፡፡
ምሁራን በሂደቱ ከመሳተፍ መታቀባቸው በሀገራችን ያሉ ችግሮችን የሚያባብስ እንጂ የሚፈታ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽነር አምባዬ በማብራሪያቸው የምሁራን በሂደቱ መሳተፍ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በምክክር ሂደቱ ላይ ጥንካሬን እንዲያዳብር እንደሚያደርግ ጠቁመው ሁሉም ሀገራዊ መግባባት ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ አሳስበዋል፡፡
በሊያት ካሳሁን