ምክር ቤቱ ስድስት ረቂቅ አዋጆችን ምርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ

You are currently viewing ምክር ቤቱ ስድስት ረቂቅ አዋጆችን ምርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ

AMN- መስከረም 30/2017 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 1ኛ መደበኛ ስብሰባው ስድስት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ የኤልክትሮኒክስ ፊርማ ማሻሻያ አዋጅ ህጋዊ ዕውቅና ለመስጠት እና በዲጂታል የፊርማ ስርዓት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ሚና መብት እና ግዴታ ለመደንጋግ የረቂቅ አዋጁ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ለምክር ቤቱ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚው ያላትን ዝግጁነት ለማረጋገጥ እና በዘርፉ መልካም እድሎችን ለመጠቀም ረቂቅ አዋጁ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ የረቂቅ አዋጁን መሻሻል ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅምና ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በጥልቀት ሊያየው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ፤ አዋጅ ቁጥር 1/2017 ሆኖ ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነት እና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ የኢትዮጵያ የህንፃ ረቂቅ አዋጅ የአገልግሎት ለውጥ ሥራ የሕዝብን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ እና የህንጻ ተደራሽነትን ለአካል ጉዳተኞችና ለማህበረሰቡ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አመልክተዋል።

እያጋጠሙ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ የግንባታ ጥራት እና የሃብት ብክነት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ግልፅና ምቹ የሆነ የአሰራር ስርዓትን ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤በከተሞች የሚገነቡ ህንፃዎች የመሬት የመሸከም አቅም፤ የአካል ጉዳተኞችን ደህንነት እና የአካባቢን ተፅዕኖ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ረቂቅ አዋጁም አዋጅ ቁጥር 2/2017 ሆኖ ለዝርዝር እይታ ለከተማ፣ መሰረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

የእንስሳት ጤና እና ደህንነት ረቂቅ አዋጅ በእንስሳት ሃብት ልማት የህዝቡን ተጠቃሚነትና በዘርፉ ዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር እና ደህንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርትን ለማሳደግ እና ለማሻሻል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ አመልክተዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ዜጎች በእንስሳት ሃብት ልማት ተጠቃሚ እና ጤናማ የኑሮ ዘይቤ ለማፍጠር ያስችል ዘንድ በህግ ማዕቀፍ ማካተቱ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 3/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ፤ የመድኃኒት ፈንድና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለጤና፤ ማህበራዊ ልማት፤ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 6/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለከተማ፣ መሰረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መምራቱን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review