ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህር ዳር ከተማ አሁናዊ ገፅታ አስመልክተው ያሰፈሩት መልዕክት፡-

You are currently viewing ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህር ዳር ከተማ አሁናዊ ገፅታ አስመልክተው ያሰፈሩት መልዕክት፡-
default

የጣና ዳር ንግሥቷ፣ ባለዘንባባዋ ሙሽራ፣ የቱሪዝም አስኳሏ ባህር ዳር ስራ ላይ ነች፡፡

ፍፁም የሰላም አየር፣ የዓይንና የመንፈስ ማረፊያ ውብ ሥፍራ የታደለችው ባህር ዳር ከመዝናኛ እስከ ግዙፍ የንግድ ስፍራዎቿ በእንቅስቃሴ ተሞልተዋል፤ ሀገሬው ከጧት እስከ ማታ ሥራ ላይ ነው፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከልጅ እስከ አዋቂ በልዩ ልዩ ስፖርቶች ደምቀዋል፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ግዙፉ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርጋት ይሆናል።

ሀገሬው በሥራ የደከመ አካሉንና አዕምሮውን ለማደስ ስፖርት ሲሠራ፣ በመዝናኛ ማዕከላት ሲዝናና፣ በዘንባባዋ ጥላ ስር አረፍ ሲል፣ በጣና ዳርቻ ሰብሰብ ብሎ ሲጫወት፣ በምሽት በእግር ሲንቀሳቀስ ማየት ልብን ሀሴት ያወርሳል።

ወቅቱ የዐቢይና የረመዳን አፅዋማት የሚፆሙበት ነው።

የከተማዋ ምዕመን ሰርክ ወደ መስጂድና ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሲተምም ማየት መንፈሳዊ ኩራትን ይፈጥራል።

ውቧ ከተማ ልማቷን እያፋጠነች፣ ፍፁም የሰላም ድባብ፣ እረፍት አልባ የልማት ሥራ፣ ሞቅ ያለ የመዝናኛና የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይባት ሆናለች።

ባየነው የሠላም ንፋስ የልማትና የሥራ ጥድፊያ እንዲሁም የቱሪዝም መነቃቃት ተደሰተናል።

የተጀመሩ ስራዎችን ዓይናችንን ሳንነቅል በተገቢው ጥራት እንዲጠናቀቁ ክትትላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

AMN – መጋቢት 10/2017

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review