“ምክክርን ገንዘብ ስናደርግ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይታወጃል”

You are currently viewing “ምክክርን ገንዘብ ስናደርግ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይታወጃል”

                                             የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)  

የሰው ልጅ የፈጣሪን ህግ በመተላለፉ ሞት ተፈርዶበት፣ በዕዳና በባርነት ሰንሰለት ታስሮ ይኖር ነበር፡፡ አዳምና ሔዋን በበደላቸው በመፀፀታቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሰቀል፣ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳት እንደሚያድናቸው በነቢያት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፡፡ ጊዜው ሲደርስም በዕለተ አርብ መስቀል ላይ ተሰቅሎ፤ በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ፡፡ ይህቺ ዕለትም “ትንሳኤ” እየተባለች እንደምትጠራ የክርስትና ሃይማኖት አባቶች ያስተምራሉ፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የሰው ልጅ ከሞት ወደ ህይወት የተሸጋገረበት፣ ከባርነት ወጥቶ ነጻነትን፣ ከጨለማ ህይወት በብርሃን መኖርን፣ ሰላምና ተስፋ ያገኘበት ነው፡፡ ልክ እንደ ክርስቶስ ትንሳኤ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ከግጭት አዙሪት መውጣት፣ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና እድገት እንዲመጣ ይሻል፡፡ ዘመናዊ የፓርቲ ፖለቲካ ከተጀመረበት ወዲህ ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያሳየው ግን ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በውይይትና ምክክር የመፍታት ባህል አለመታየቱ ነው፡፡

በዚህም የተነሳ ልዩነቶች ከመጥበብ ይልቅ እየሰፉ፣ ወደ ግጭት እያመሩ መጥተዋል፡፡ በየጊዜውም በሚፈጠረው ግጭት ህዝብ ብዙ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። አልፎ ተርፎም የሀገር አንድነትና ህልውና እየተፈተነ ነው፡፡

ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ እንደሆነ የሚናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ነዋሪ ሀምሳ አለቃ መኮንን ደርሰህ፣ በረጅሙ የህይወት ዘመናቸው ችግሮችን በንግግርና ውይይት ከመፍታት ይልቅ በውጊያ ወይም የሀይል አማራጭን በመከተል ለመፍታት ሲሞከር ነው የማየው፡፡ ይህ አካሄድ ውጤት ሲያመጣ አልታየም፤ ይልቁንም ሀገራችንን ከድህነትና ኋላቀርነት እንዳትወጣ አድርጓል ሲሉ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንደሌለን ያስረዳሉ፡፡

ሀምሳ አለቃ መኮንን እንደገለፁት፤ እንደ ሀገር አለመግባባቶችን በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊደግፈው ይገባል። አሁን የተገኘውን ዕድል ያልተጠቀመ ሌላ እንዲህ ዓይነት ዕድል ሊያገኝ አይችልም ወይም ቢያገኝም ሊጠቀም አይችልም፤ ስለዚህ ሁሉም አካል ሰላም ለማምጣት የተመቻቸውን አማራጭ መጠቀም አለበት ብለዋል፡፡

የአየር ጤና አካባቢ ነዋሪው ወጣት ጴጥሮስ ጌታዬ በበኩሉ በኢትዮጵያ የሚፈጠር የሰላም እጦት በእጅጉ እንደሚያሳስበው ይናገራል፡፡ ሁሉም ወገን ከሀገር ይልቅ የራሱን ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት ግጭት እየተፈጠረና የሀገር አንድነት እየተጎዳ መጥቷል፡፡ ሁሉም በየአካባቢው የመንደር አለቃ ሆኖ ሰላምን ማምጣት አይቻልም፡፡ የሀሳብ ልዩነቶች ካሉ ሊፈቱ የሚገባቸው በመነጋገርና በመወያየት እንደሆነ ይገልፃል፡፡

ኢትዮጵያ ያላት ሀብት ከራሷ አልፎ ለሌላውም የሚተርፍ ነው፡፡ የጠፋውን ዘላቂ ሰላም ለማምጣትም የተያዘው ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊ ነው። በሰላም ጉዳይ የማይመለከተው አካል ስለሌለ፣ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን እያንዳንዱ ሰው ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚጠበቅበት የሚናገረው ወጣት ጴጥሮስ፣ በተለይ ወጣቱ ማንኛውንም ነገር ማድረግ የሚያስችል እምቅ አቅምና ኃይል አለው፡፡ ይህንን ሰላምን ለማምጣት ከሚጥሩ ወገኖች ጎን በመሆን ሊያውለው እንደሚገባ አብራርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንዳብራሩት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገር በቀል እውቀትን መሰረት በማድረግ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በየትኛውም ቦታ የሚካሄዱ የምክክር መድረኮች አስቀድሞ በሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የባህል መሪዎች ጸሎት (ዱአ) እና ምርቃት ነው የሚከፈቱት፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ከ98 በመቶ በላይ አማኝ ነው፡፡ ሃይማኖተኝነት፣ ፈጣሪን የመፍራት፣ የመከባበር፣ የመተዛዘን፣ የመደጋገፍ ባህላዊ እሴት አሉት። እነዚህ እሴቶች ኢትዮጵያውያንን ለሺህ ዘመናት እንደ ክር በማስተሳሰር በአንድነት እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል፡፡ በሀገራዊ ምክክሩ ባህላዊ እሴቶችን ወደ ወረት ወይም ካፒታል በመቀየር ሀገርን ለማሻገር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመከባበር፣ ዝቅ በማለት፣ በመደማመጥ፣ ችግሮችን መፍታት፣ ህይወትን ማደስ ይቻላል፡፡  አንዱ ሌላውን በጠላትነት በመፈረጅ፣ ሌላውን “ጨለማ”፤ ራስን “ብርሃን” በማድረግ ሳይሆን ጨለማውን ብርሃን ሊያሸንፈው የሚችለው እውነት ሲወጣ መሆኑን ተረድተን፤ የእውነት ፍለጋ አካል የሆነው ምክክርን ገንዘብ ስናደርግ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይታወጃል፡፡

ኮሚሽነር ዮናስ፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ወይም ድል በዋናነት አንዳችን ሌላችንን ስናከብር፤ ስንታዘዝ፣ ስንተዛዘን፣ ስንደማመጥና ስንመካከር የሚመጣ ነው፡፡ የነበሩ ቁስሎቻችንን ማከም የምንችለው ካለፈው ትምህርት በመውሰድ፣ ይቅር በመባባል ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ አንዳችን ሌላ ቦታ ሆነን ችግሩን በመረዳት፣ ቁርሾዎችን ከውስጥ በማውጣት፣ ይቅር በመባባል፤ ዳግም ወደኋላ ላለመመለስ ቃል በመግባት፣ ራሳችንን የምናድስበት ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በምክክሩ የህዝብ ተሳትፎ

ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን አሳታፊነትና አካታችነትን መርህ በማድረግ እየተካሄደ እንደሚገኝ ዮናስ (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትም እንደ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ የሚለያይ ሆኖ አስር የሚደርሱ ህዝብን የሚወክሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ማለትም፡- ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ምሁራን፣ የመንግሥት እና የግል ድርጅት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ በባህል እና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ ማህበረሰቦች እንዲሁም ተፈናቃዮች ይሳተፋሉ፡፡

ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወጣቶችን ብናነሳ፣ በየትኛውም ሀገር በሚፈጠር ግጭት፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ግንባር ቀደም ተዋናይ ናቸው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ለወጣቶች ብሩህ ተስፋ የምትሰጥ፣ ጥለዋት የሚሰደዱባት ሳይሆን ሌሎች ለመምጣት የሚመኟት ሀገር ለመፍጠር ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተካሄዱ የአጀንዳ ሀሳብ የማሰባሰብ ሂደቶችም በተሳታፊነት፣ በአመቻችነት፣ በበጎ ፈቃደኝነት፣ በአመራርነት ግንባር ቀደም በመሆን የድርሻቸውን መወጣታቸውን ኮሚሽነር ዮናስ ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው በአንድ ሀገር የሰላም እጦት ሲፈጠር በቀዳሚነት ሰለባ የሚሆኑት፣ ግማሽ የሚሆነውን የማህበረሰብ ክፍል የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው። ከሚሽነር ዮናስ እንደሚገልፁት፣ በኢትዮጵያ በነበረው በባህል ተፅዕኖ፣ ሴቶች ከውሳኔ ሰጪነት ተገልለው ነው የቆዩት፡፡ በምክክሩ ወደ ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡና ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ተሰርቷል፡፡ በኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ በነበሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በአማካይ ከ40 በመቶ በላይ ድርሻ ይዘዋል፡፡ የኮሚሽኑ ፍላጎት 50 በመቶ ማድረስ የነበረ ቢሆንም አሁንም ያሳዩት ተሳትፎ የሚበረታታ ነው፡፡ በሌሎች አነስተኛ ተሳታፊ በታየባቸው አካባቢዎችም ቀስ በቀስ መሻሻል እየታየ ነው፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በየአካባቢው ሰላምና እርቅን በማስፈን፣ ሀገርን በማቆየት ባለውለታ የሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ እንደሚገኝም ኮሚሽነር ዮናስ ያነሳሉ፡፡ በተሳታፊነት ያልገቡ ሽማግሌዎች በአማካሪነትና ተፅዕኖ በመፍጠር ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችም በምክክሩ ሂደት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ቀጣይ ምን ይጠበቃል?

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን እያጠናቀቀ ይገኛል። በትግራይ ክልል፣ በፌዴራልና በዳያስፖራ ደረጃ አጀንዳዎች ከተሰበሰቡ በኋላ ምክክር የሚደረግባቸው አጀንዳዎች በኮሚሽኑ ምክር ቤት ይቀረፃሉ፡፡ በመቀጠልም ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ይደረጋል። በምክክሩ ስምምነት የተደረሰባቸው ምክረ ሀሳቦች ተለይተው ለመንግስት ይቀርባሉ፡፡

ኮሚሽነር ዮናስ እንደሚያስረዱት፣ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ሶስት ዓላማዎች አሉት፡፡ ሀገራዊ መግባባትን ማምጣት፣ በህዝብና በመንግስት እንዲሁም በህዝብና ህዝብ መካከል መተማመን እንዲፈጠርና ምክክር ባህል እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የምክክሩ ሂደትና ከምክክሩ የሚገኘው ውጤት በአግባቡ እንዲተገበር የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች እንዲተገበሩ ምክረ ሀሳቦችን ለመንግስት ያቀርባል፤ ህዝብም እንዲያውቀው ያደርጋል፡፡ በዚህን ጊዜ የተሰጡ ምክረ ሀሳቦች ስራ ላይ እንዲውሉ ህዝብ ግፊት ማድረግ ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ህዝብ የስልጣን ምንጭና ባለቤት ነው፡፡

“በየአካባቢው በመመካከር ውሳኔዎች እንዴት ስራ ላይ ቢውሉ የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል?” በሚለው ላይ ህዝቡ ወደፊት መምጣት አለበት። እስከ አሁን ሊሂቃን ከላይ ሆነው የሚሰጡትን ብቻ ሲቀበል ነው የነበረው፤ በምክክሩ ሂደት እያደረገ እንዳለው ተሳትፎ በትግበራው ላይም ወሳኝ ሚና መጫወት  እንዳለበት ኮሚሽነር ዮናስ አስገንዝበዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነፃነት ላይ የተቃጡ ጥቃቶች ማክሸፍ፤ የሀገርን ዳር ድንበር ማስጠበቅ የተቻለው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ባለቤት ሆኖ በመሳተፉ ነው። በሀገራዊ ምክክሩም ህዝቡ በባለቤትነት ተሳትፎ እንዲያደርግ መገናኛ ብዙሃን ግንዛቤ በማስጨበጥ እየተጫወቱት ያለውን ሚና አጠናክረው መጠቀል ይኖርባቸዋል፡፡ ሀገራዊ ምክክር በብዙ ዓመታት አንዴ የሚገኝ እድል ነው፡፡ መንግስትን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማህበራትን፣ ዕድሮችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ መምህራንን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች  በንቃት እየተሳተፉ ነው፡፡ በምክክሩ ሂደት በተለያየ ምክንያት ወደኋላ ያሉ ወይም እየተሳተፉ የማይገኙ አካላት በቡድን ወይም በግለሰብ አጀንዳ በመስጠት ወርቃማውን እድል መጠቀም ይኖርባቸዋል ሲሉም ኮሚሽነር ዮናስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ በፈቃዱ ዳባ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እና በኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማሲ አስተምረዋል። በሶማሊላንድ  ሃርጌሳ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ዓመታት ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ እሳቸው እንደሚናገሩት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካል፤ ያለምንም መሳቀቅና ፍርሃት ሀሳቡን የሚያንሸራሽርበት ዕድል ማመቻቸት ይገባል፡፡ በሂደቱ ታጥቀው ጫካ የገቡ ሀይሎች ሀሳባቸውንና አጀንዳዎችን እንዲያቀርቡ በተቻለ መጠን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ በፈቃዱ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ባህል ሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ልዩነትን በመደማመጥ የመፍታት ባህል የለም፡፡ መደማመጥ፣ መነጋገርና መደራደር ካልቻልን የሀገር ችግር ሊፈታ አይችልም፡፡ ለሀገር ሲባል መሸነፍ፣ መደማመጥ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ሀገራዊ ምክክር ደግሞ ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ መንገድ በመሆኑ በአግባቡ  ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን መቀራረብ፣ መነጋገር፣ መተማመንን የሚያሳድጉ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልግም የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ በፈቃዱ ያነሳሉ፡፡ ለምሳሌ መንግስት ከተለያዩ የታጠቁ ሀይሎች ጋር ድርድር አድርጎ ወደ ሰላም የተመለሱ አሉ፡፡ ቀጣይም የሚደረጉ ድርድሮች ውጤታማ ከሆኑ ሌሎችም የሰላምን አማራጭ ሊመርጡ ስለሚችሉ በዚህ ረገድ ጠንካራ ስራ ይጠበቃል፡፡

ችግሮችን በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ በመመካከር መፍታት ካልተቻለ ከግጭት መውጣት አይቻልም፡፡ ግጭቶች ሲፈጠሩ አቅመ ደካሞችን፣ ሴቶችንና ህፃናትን ጨምሮ አብዛኛው ማህበረሰብ የችግሩ ተጠቂ ነው፤ ልዩነቶችና ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱም ፍላጎት እንዳለው የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ በፈቃዱ ያነሳሉ፡፡

በሀገር ጉዳይ የማይመለከተው የለም። ሀገር ሰላም ካልሆነ መማር፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ስራ መስራትና መፍጠር አይቻልም፡፡ ከዚህ አኳያ ለሀገር ሲባል ሆደ ሰፊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ህልውናዬ፣ የልጅ ልጆቼ እጣ ፈንታ በሀገር ሰላም ላይ የተመሰረተ ነው ብሎ በማመን፣ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን በጎ ተፅዕኖ በባለድርሻ አካላት ላይ መፍጠር እንደሚያስፈልግም  አስገንዝበዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review