ህንድ ከአስደንጋጩ የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ገና አላገገመችም፡፡ በተለይ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች ነፍሳቸው ልታርፍ አልቻለችም፡፡ ሕልፈቱ እንዳለ ሆኖ አካላቸውን ማሳረፍ አለመቻላቸው ሰላም ነስቷቸዋል፡፡
በአንድ በኩል የአደጋው መንስኤ እንዲጣራላቸው ይወተውታሉ ፤ በሌላ በኩል የሟቾች አስክሬን ተለይቶ እንዲሰጣቸው ጫና እየፈጠሩ ይገኛል፡፡
አሁን በተሰማው ዜና ባለፈው ሃሙስ በተከሰከሰው 787 ቦዪንግ ድሪም ላይነር ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ 270 ሰዎች አስክሬን መገኘቱ ተነግሯል፡፡ አህመድአባድ በሚገኘው የህዝብ ሆስፒታል የሚሰሩት ዶክተር ዳቫል ጋምቲ ይህን ቁጥር አረጋግጠዋል፡፡ ለባለሞያዎቹ ትልቅ ችግር የሆነባቸው አንዱን ከሌላው መለየት ላይ ነው፡፡
ከአደጋው አስከፊነት መነሻ ሟቾቹን ለመለየት የዘረመል (DNA) ምርመራ እያደረጉ እንደሆነ ዶክተር ዳቫል ተናግረዋል፡፡ ማንነትን ለመለየት የሚደረገው ምርመራ ቢያንስ 72 ሰዓታት እንደሚያስፈልጉትም አያይዘው ገልፀዋል፡፡
አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት አካባቢ የነበሩ እና ሕይወታቸውን ያጡ 10 ሰዎች ለቤተሰቦቻቸው እንደተሰጡም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ለተዓምር የተረፈው ቪሽዋሽ ኩማር ራምሽ አሁን በተሻለ ጤንነት ላይ ይገኛል፡፡ ዶክተር ዳቫል ጋምቲ በፈለገው ሰዓት ወደ ቤቱ ማቅናት ይችላል ብለዋል፡፡
አጠቃላይ መረጃ የሚገኝበትን ጥቁር ሳጥን ያገኘው የህንድ መንግስት የአውሮፕላኑን መከስከስ አደጋ ምክንያት አብጠርጥሬ ለመመርመር ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡