
AMN- ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም
ረሃብን ለማስወገድ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት ላለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በቆየው ከረሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ ከአስርት ዓመታት በፊት አስከፊ የረሀብ አደጋ አጋጥሟት እንደነበር አውስተው፥ ዛሬ ላይ ያንን መጥፎ ታሪኳን የሚቀይር አኩሪ ጉዞ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።
በመሪዎች ሀሳብ አመንጪነት እና ቆራጥ የተግባር እርምጃ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ስኬቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ በማንሳት።
ጉባኤው የዓለም የምግብ ስርዓት ላይ ያሉ ችግሮች እና መፍትሔዎች የተለዩበት ስኬታማ መድረክ እንደነበርም ገልጸዋል።
የሀገራትን የምግብ ዋስትና እና የዘላቂ የልማት ግቦች ለማረጋገጥ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ወሳኝ እንደሆነም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ረሃብን ከዓለም ለማስወገድ በአፋጣኝ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸውን ወሳኝ እርምጃዎች ዘርዝረዋል።
አንደኛው ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚከናወኑ ሥራዎች ህዝብን ለማስተባበርና ለማሳተፍ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ በቂ የሆነ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ነው ብለዋል።
ከሁሉ በላይ ከረሃብ ነፃ ዓለም ለመፍጠርና ተግባራዊ እርምጃዎችን ወደ ውጤት ለመቀየር ባለራዕይ መሪዎችን ማብዛትና ትርክትን መቀየር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካን እምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም አስከፊውን ረሃብ ለማስወገድ በአንድነት መነሳት ለነገ የማይባል መሆኑን ጠቅሰው፥ ማንም በረሃብ እንዳይጎዳ አፋጣኝ የተቀናጀና ተግባራዊ እርምጃ ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!