ሩሲያ ለመፃዒው የአፍሪካ ዘመን ያላት ቀና ራዕይ..

You are currently viewing ሩሲያ ለመፃዒው የአፍሪካ ዘመን ያላት ቀና ራዕይ..

በብዙ ፅንፍ በተወጠረችው ዓለም የአፍሪካ ሚና ጎልቶ እንዲወጣ እና እኩልነት እና ሉዓላዊነትን በማክበር ላይ የተመሠረተ ትብብር አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ፅሑፍ በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዲፓርትመንት በኩል ታትሞ ለህትመት በቅቷል፡፡

የፅሑፉ አዘጋጅ የሆኑት በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዳይሬክተሩ አሌክሴ ዶርቢኒን፣ ሩሲያ በብዙ ፅንፍ በተወጠረችው ዓለም ውስጥ አፍሪካ ወሳኝ ሚና ሊኖራት በሚያስችል መልኩ እራሷን መገንባት ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2023 ጥቅምት ወር ላይ በሞስኮው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተቋም አዘጋጅነት በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ፎረም ላይ በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አናቶሊ ባሽኪን “በአፍሪካ አህጉር ሥር የሚገኙ ሀገራት ትክክለኛ ሉዓላዊነትን እንዲያገኙ እና ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርሕ መሰረት የምዕራቡን ዓለም ፖለቲካ ዘመም መፍትሔ እና ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል ሩሲያ ድጋፍ ታደርጋለች” ማለታቸውም የሚታወስ ነው፡፡

“የአፍሪካን አንድነት ማጠናከር” የሚለው የፅሑፉ አንኳር ጉዳይ ሲሆን በዚህም ሩሲያ በአፍሪካ ህብረት የሚንፀባረቀውን የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን ትደግፋለች፡፡

እንደ ፀሀፊው ገለፃ የአፍሪካ ህብረት ማለት የአፍሪካ ድምጽ በዓለም ደረጃ  የሚደመጥበት መድረክ ነው፡፡

“የአፍሪካ ህብረት የፓን-አፍሪካ እንቅስቃሴ መገለጫ ነው፤ እንቅስቃሴው ሀገራትን በአህጉር ደረጃ ያዋሀደ እና ሁሉንም አፍሪካዊያንን በመወከል በፖለቲካው ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተደማጭነት እየጨመረ እንዲመጣ ያስቻለ ነው ” ሲሉ ለንባብ ባበቁት ፅሑፍ  አትተዋል፡፡

የቅኝ ግዛት ውርሶችን ማውገዝ የፅሑፉ ሁለተኛው ዐቢይ ትኩረት ነው፡፡ ሩሲያ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ በሀገራት ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጫና የሚያደርሰውን የኒውኮሎኒያሊዝምን እሳቤ አጥብቃ ታወግዛለች፡፡

“አፍሪካ በቅኝ ግዛት በእጅጉ የተጎዳች አህጉር ናት፤ ያላት ቁሳዊ እና የሠው ሀብት ለዘመናት በአውሮፓዊያን ተብዝብዟል” ይላል አሌክሴ ዶርቢኒን በጽሑፉ፡፡

አፍሪካን እንደ አንድ የኃይል ማዕከል መደገፍ የሚለው ደግሞ ሶስተኛው የጽሑፉ ማጠንጠኛ ጉዳይ ነው፡፡ ከአፍሪካ ጋር ትብብርን ማጠናከር በሩሲያ የውጭ ጉዳይ  ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን የሚገልጸው ጽሑፉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “በዓለም እድገት ውስጥ አፍሪካ ሁነኛ እና ወሳኝ የልማት ማዕከል ናት” ማለታቸውንም ይጠቅሳል፡፡

አራተኛው ነጥብ ወዳጅነትን ከአፍሪካ ጋር ማጠናከር የሚለው ሲሆን በዚህም አፍሪካ አንድም ፀረ-ሩሲያ የሆነ አቋም የያዘ ሀገር የላትም ሲል ያትታል፡፡

አንድም በአህጉሪቱ የሚገኝ ሀገር ፀረ-ሩሲያ የሆኑ ማዕቀቦችን ሲደግፍ አልታየም፣ ይልቁንም በተመባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በምዕራቡ ዓለም የሚደገፈውን የፀረ-ሩሲያ  አጀንዳዎችን አፍሪካ እንደማትቀበል ዳይሬክተሩ አመልክቷል፡፡

ታሪካዊ ትስስርን መነቃቃት ሌላኛው የጽሁፉ ሀሳብ ነው፡፡ አሁን ጊዜው ሩሲያ ፊቷን ወደ አፍሪካ የመለሰችበት እና የተረሱ ትስስሮችም የሚታደሱበት መሆኑንም ይገልጻል፡፡ ለዚህም ቀደም ሲል ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር የነበራትን አሀዛዊ የንግድ ግንኙነት መረጃዎችን በአብነት ያነሳል፡፡

በፈረንጆቹ 1985 የሶቪዬት ህበረት ከአፍሪካ ጋር የ9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ትስስር ነበራት፡፡ ይሁንና ይህ አሀዛ በ1995 ላይ ወደ 0 ነጥብ 98 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሎ እንደነበር ጽሁፉ አስታውሷል፡፡

በወቅቱ በርካታ የሩሲያ ቆንፅላ እና ኤምባሲዎችም በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የጠበቀ ግንኙነት የነበራቸው ናቸው፡፡

አሁን ደግሞ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በተደጋጋሚ ወደ አፍሪካ ሀገራት የሚያደርጉት ጉዞ ሩሲያ ከአህጉሪቱ ጋር የነበራትን ታሪካዊ ትስስር ለማጠናከር በተግባር ያሳየችበት ነው ይላል ጽሁፉ፡፡

አጋርነትን በእኩል ማስቀጠል የፅሑፉ ስድስተኛው ነጥብ ሲሆን አፍሪካ ቁልፍ ችግሮቿን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ሩሲያ አቅም ያላት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review