
ሩሲያ እና ዩክሬን በፍጥነት የተኩስ አቁም ንግግር እንደሚጀምሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ ይህን የተናገሩት ትናንት ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ጦርነቱን ማስቆም በሚቻልበት አግባብ ላይ በስልክ ከተወያዩ በኋላ ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለሁለት ሰዓት ያህል ከቆየው የስልክ ውይይት በኋላ ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን “ጊዜ ሳይወስዱ” ወደ ተኩስ አቁም ድርድር እንደሚገቡ አስታውቀዋል፡፡
ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁን የገለጹት ትራምፕ ፤ በሀገራቱ መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን “በፍጥነት ደርድር መጀመር ይገባል” ብለዋል፡፡
ትራምፕ ከፑቲን በተጨማሪ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጋር በሰላም ድርድሩ ዙሪያ መወያየታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከፑቲን ጋር ካደረጉት የስልክ ውይይት አስቀድሞ ፤ ውይይቱ በዩክሬን ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም አይነተኛ መፍትሄ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡