
AMN – ግንቦት 1/2017 ዓ.ም
ከስፔናዊ እናታቸው እና የፈረንሳይ እና ጣልያን ደም ካላቸው አባታቸው በቺካጎ በ1955 የተወለዱት የ69 ዓመቱ ፕሪቮስት በ1982 ቅስናቸውን ተቀብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው መሪ ሲሆኑ አብዛኛውን የአገልግሎት ዘመናቸውን በደቡብ አሜሪካ ሚስዮናዊ ሆነው አሳልፈዋል፡፡ በፔሩም በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሹመት ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል፡፡
በላቲን አሜሪካ ጳጳሳትን በመምረጥ እና በመሾም ቁልፍ ሚና ያላቸው የጳጳሳት አለቃ ሆነው በማገልገላቸውም ይታወቃሉ።
በቅርቡ ያረፉት ሊቀ ጳፓስ ፍራንሲስ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2023 ኤጲስ ቆጶስ ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ካርዲናል አድርገው ሾመዋቸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሮበርት ፕሬቮስት 267ኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው፣ ስለ ሰላም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በሞት ለተለዩት የቀድሞው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ያላቸውን ክብርም ገልፀዋል።
የዓለም መሪዎችም ለአዲሱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ የእንኳን ደስ አሎት መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ማግኘት ትልቅ ክብር ነው ሲሉ አስተያየት መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በሊያት ካሳሁን