በዛሬው ዕለት ሩሲያ እና ዩክሬን ያደረጉት የሰላም ንግግር የጦር እስረኞችን ከመለዋወጥ ስምምነት ባሻገር ሰፊ የሐሳብ ልዩነት የተስተናገደበት ሆኖ አልፏል።
በቱርኪዬ ኢስታንቡል በተካሄደው ሁለተኛው ዙር የሀገራቱ ንግግር ላይ የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሩሲያ ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈጸም በኪዬቭ የቀረበውን ሐሳብ በድጋሚ ውድቅ ማድረጓን አስታውቀዋል።
የሩሲያ ቡድን በበኩሉ የተኩስ አቁሙ ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደባቸው በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች ከሁለት እስከ ሦስት ቀን በሚቆይ የጊዜ ገደብ ይጀመር ከማለት በዘለለ ዝርዝር ሃሳብ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ከአንድ ሰዓት በላይ በፈጀው የዛሬው የሩሲያ-ዩክሬን ንግግር ላይ ሀገራቱ በሁለቱም ወገኖች የሚገኙ የታመሙ እና በጽኑ የቆሰሉ የጦር እስረኞችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል።
በተጨማሪም ሀገራቱ ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ታሳሪ ወገኖቻቸውን ለሀገራቸው ለማብቃትም መስማማታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።