AMN-የካቲት 30/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ማምሻውን የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ ከጅማሮው አንስቶ በስኬት እስኪጠናቀቅ ድረስ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል::
መርሃግብሩን አስመልክተው ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት ፣ስንተባበርና በአንድነት ስንሰራ ስራዎቻችን ጥራት ያለው እና ውጤታማ ይሆናል ብለዋል።
ተግዳሮቶችን በመሻገር የጎደለውን እየሞላን ሀገራችንን ከፍ የሚያደርጉ ትላልቅ ስራዎች ለመስራት አቅም እየፈጠርን ሁላችንም ለስኬት እንደምንበቃ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል::
ከንቲባ አዳነች፣ ማዕከሉ ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና ለሀገር ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ለስኬት እንዲበቃ አስተዋጽዖ ያበረከቱ የማዕከሉ የቦርድ እና የማኔጅመንት አባላት፣የስራ ተቋራጩ እና አማካሪ ድርጅቱ፣ ባለአክሲዮኖች፣ ለልማት ከአካባቢው የተነሱ ነዋሪዎችን እንዲሁም ስራውን ላስተባበሩ የከተማዋ አመራሮች እና ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።