ስንዴ በእርዳታ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው በዋናነት በኢትዮጵያ ላሉ ስደተኞች ነው:-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ስንዴ በእርዳታ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው በዋናነት በኢትዮጵያ ላሉ ስደተኞች ነው:-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ግንቦት 29/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከ1 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ያሉባት ሀገር በመሆኗ የተለያዩ የዓለም ሀገራት በዋናነት እነዚያን ስደተኞች ለመደገፍ ሲሉ ስንዴ በእርዳታ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፣ ከውጭ የሚገባን ስንዴ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ስንዴ በከፍተኛ ደረጃ እያመረተች መሆኑን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በመሆኑም ላለፉት ሦስት ዓመታት ለስንዴ ግዢ ገንዘብ አውጥታ እንደማታውቅም ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በውስጧ ያሉ ስደተኞችን በክብር ከመያዝና ከማስተማር ባለፈ ሁሉን ቀልባ ስለማትችል ሌሎች ሀገራት የመመገብ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ ባለፈ እራሳቸውም አምራች ሆነው ተመሳሳይ ምርት ከሌሎች ሀገራት ወደ ሀገራቸው እንደሚያስገቡ እንደ ማንኛውም ሀገራት ስንዴም ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ እያስገባች እንጂ እያመረተች አይደለም ሊያስብላት እንደማይችል አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና አምራች ሀገር ሆና ቡና ከውጭ ታስገባለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ተጠቃሚው አማራጭ ስለሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሁን ባለው የንግድ ሥርዓት እንድን ሀገር ምርት እንዳያስገባ መከልከል እንደማይቻል በማንሳትም፣ ከውጭ የሚገባ ምርት ቢኖርም ዜጋው የራሱን ምርት ሊያስቀድም እንደሚችል ነው ያመለከቱት፡፡

ለዚህ ሀሳብ ማጠናከሪያም አሜሪካ በዓለም ግንባር ቀደም የመኪና አምራች ሀገር ሆና ሳለ፣ የዜጎችን መርጦ የመግዛት እድል ለማስፋት፣ ከሌሎች ሀገራት መኪኖች እንዲገቡ እንደምትፈቅድ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review