ቀደምት የህትመት ውጤቶች በትንሳኤ ሰሞን

You are currently viewing ቀደምት የህትመት ውጤቶች በትንሳኤ ሰሞን

ዛሬ ላይ በጋዜጣዎች የሚወጡ የዜና ዘገባዎች ወደ ፊት የታሪክ ግብዓት ይሆናሉ፡፡ በተለይ የዘመኑ የአኗኗር ዘይቤና መንፈስ ምን ገጽታ እንደነበረው በማሳየት ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው መሆኑ በታሪክ ተመራማሪዎችም ሆነ ስለ ዘመኑ ማወቅ በሚሹ ሰዎች ዘንድ እጅግ ተፈላጊ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ፣ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ወደ ኋላ ተጉዞ የትንሳኤ በዓል አከባበር ዋዜማ፣ ዕለትና ማግስት ምን ይመስል እንደነበር ከቀደምት ጋዜጣዎችና መጽሔቶች መካከል ጥቂቶችን ቃኝቷል፡፡

“ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ በሚያዝያ 23 ቀን 1922 ዓ.ም እትሙ ላይ “የስቅለትና የትንሳኤ በዓል  በግሪክ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ የሚከተለውን ዘገባ አስነብቧል። ዘገባውም፣ “የአክሱም ጳጳስ ፓትርያርክ ኒኮላ ቀድሞ እዚህ የነበሩት አሁን ደግሞ እንደገና ወደ አዲስ አበባ መጥተው ዓርብ በሶስት ሰዓት በዓለ ስቅለትን ለማክበር ግሪካውያንም ሁሉ በቤተ ክርስቲያናቸው ተሰብስበው መብራት አብርተው ዑደት አደረጉ፡፡ ፓትርያርክ ኒኮላም ስለ ኢትዮጵያና ስለ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ፣ ስለ ልዕልት ወይዘሮ መነንና ስለመኳንንቱ፣ ስለ ሕዝቡ ሁሉ ፀሎት አደረጉ፡፡ በበዓለ ትንሳዔም እንደዚሁ በከተማ ያሉ ግሪካውያን ሁሉ ተሰብስበው ፓትርያርክ ኒኮላስ ቀድሰው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ተናገሩና ሕዝቡን ደስ አሰኝተው አሰናበቱት” ይላል፡፡

በዚሁ ዓመት በዋለው የትንሳኤ በዓል፣ ዕለቱን በተዘዋዋሪ መንገድ ሽፋን እንዲያገኝ ያደረገ ጉዳይ ተከስቷል፤ የእሳት አደጋ፡፡ እንዲህ ሰፍሯል፤ “ሚያዝያ 20 ቀን ከምሽቱ በሶስት ሰዓት ሱቁን ዘግተው ሰራተኞች ከወጡ በኋላ ሙሴ ኮርስቶና፡ ሙሴ ጆርጂና ካሉ ጆርጥሎስ ወንድማማቾቹ የሚነግዱበት የወይዘሮ በለጥሻቸውና የደጃዝማች መሸሻ ወርቄ ሱቅ ተቃጠ። የተቃጠለው ዕቃ ሂሳብ እስከ 2ሺ ብር ይሆናል፡፡ ትጉሁ ከንቲባ ነሲቡ ዘበኛውን በጥሩንባ አስነስተው ከእሳት ያዳኑት ዕቃ 2ሺ ብር ይገመታል። ሲቢርቶ የነበረበት ጓዳ እንዳይቃጠል በጎረቤት የነበሩ ዘበኞች ውሃ እየቀዱ በብርታት ባያጠፉት በተራው ያለ ሱቅ ሁሉ አይተርፍም ነበር። …  ቀዳማዊ ንጉስ ነገስት ኃይለሥላሴም እጅግ አዝነውላቸው የተቃጠለውን ሱቅ አይተው አይዟችሁ ብለው ተስፋ ሰጥተዋቸዋል” በማለት ዕለተ-ትንሳኤ ከእሳት አደጋ ክስተት ጋር በማስተሳሰር በጋዜጣዋ  ሽፋን አግኝቷል።

ሌላው የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ የቃኘነው በአጼ ኃይለሥላሴ ባለቤት፣ በእቴጌ መነን ስም የተሰየመውን “መነን” መጽሔት ነች፡፡ ለአብነት በሚያዝያ 16 ቀን 1962 ዓ.ም እትሟ የፋሲካ ዋዜማን የሚያስታውሱ የተለያዩ ጽሑፎች ይዛ ወጥታለች፡፡

“ሰም ለበስ” በተሰኘው የመጽሔቷ አምድ ላይ ፋሲካን የሚያስታውስ ወግ በዚህ መልኩ አስተናግዳለች፤ “አንድ ሰው ነበረ፡፡ ፋሲካ በደረሰ ቁጥር ቤቱ ተጋድሞ ያዙኝ፣ ጥለፉኝ እያለ ቤተሰቦቹን ያስቸግራል፡፡ ግን ቢያርዱት እንኳ ሐኪም ቤት አይሄድም፡፡ ታዲያ አሁን ባለፈው ፋሲካ ሰሞን እንደልማዱ ተኝቶ ምጥ የያዛት ሴት ይመስል ሲያጓራ የልብ ጓደኛው የሆነ አንድ ሰው ሊጠይቀው መጣ፡፡ የተለመደውን ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ከውጭ የመጣው ሰው እየተገረመ…“አምና፣ ካቻምናም በፋሲካ ሰሞን ታመህ ነበር፡፡ አምልኮት አለብህ ልበል?” አለና ጠየቀው፡፡

“በሽተኛው ከአልጋው ቀና ብሎ አጠገባቸው ሌላ ሰው እንደሌለ ካረጋገጠ በኋላ ‘በእውነት የታመምኩ አይምሰልህ’” አለው፡፡

“ታዲያስ?”      

“ለወላጆቼ፣ ለአያቶቼ፣ ለአማቶቼና ለጡት አባቴ ያክፋይ የሚሉትን ዕዳ መክፈል ሰልችቶኝ ነው ፋሲካ በደረሰ ቁጥር የምታመመው” አለውና ባለቤቱ ብቅ ስትል ተጋድሞ ያቃስት ጀመር በማለት ቀልድ አዘል የፋሲካ ወግ ዳስሳለች፡፡

ሌላው በዚህች መጽሔት “ሴቶች ገጽ” በተሰኘው ዓምድ ላይ፣ ብዙ ወንድም አገኘሁ በምትባል ጋዜጠኛ የተጻፈ ፋሲካን በሚመለከት ሰፋ ያለ ሃተታ ተስተናግዷል። ይህች ሃተታ በዋናነት የፋሲካ ገበያ ምን እንደሚመስል የምታስቃኝ ብትሆንም፣ እግረ መንገዷ ግን ብዙ አስገራሚ ጉዳዮች ዳስሳለች፡፡ በተለይ ከ1960ዎቹ አንስቶ የኢትዮጵያ ነባር ልማድና ወግ ምን ያህል እየተለወጠ እንደነበር ያሳያል፡፡ በዘመኑ በታተሙት የተለያዩ ልብ-ወለድ ድርሰቶች ውስጥ እንዳነበብነው በመጤውና በነባሩ ባህል መካከል የነበረው ፍትጊያና  የዘመኑ ሁኔታ እየተለወጠ መሄድን ቁልጭ አድርጋ ታሳያለች፡፡

እስኪ የወቅቱ የገበያ ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ከመጽሔቷ እንቀንጭብ፤ “በዓሉ የሚከበረው ከፍ ባለ ሁኔታ በመሆኑ የተለመደው የእህልና የሌሎቹ ዋጋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ታላቅ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ቁጥጥር የሌለበት ቅቤና ቅመሙ ሽንኩርትና በርበሬ ከተለመደው ዋጋቸው በላይ ሆነዋል፡፡ ምንም እንኳን በጊዜው ምክንያት የዶሮን ዋጋ ለማወቅ ባንችልም ማጣፈጫ የሆነው ቅቤ በንጥር ከሁለት ብር ከአምሳ ሳንቲም ወደ አራት ብር ተዛምቷል፡፡ በሚቀጥሉት ቀናቶች ወደ ከፍተኛ ዋጋ እንዳይሻገር የሚያሰጋ ነው፡፡ ምክንያቱም በሽሮና ዘይት የሰነበተው ሆድ ለአንድ ቀን ማራሻ እንኳን ገዝቶ እንዲበላ ነው” ስትል የገበያው መወደድ ታማርራለች፡፡

መጽሔቷ ቀጠል ታደርግና፣ “ከቅቤውም ተራ በዋጋው ያልተስማማን መስለን ወደ ቅመሙ ተራ አዘገምን፡፡ በዚያ አካባቢ አያሌ ሴቶች ነበሩ፡፡ ስለ ቅመሙ ዋጋ ጠየቅናቸው፡፡ እንዲያው በደፈና ‘አይጣል ነው’ ብለዋል፡፡ በእርግጥም እንደተመለከትነው ነጭና ጥቁር አዝሙድ በተለይም በሶብላና ነጭ አዝሙድ የሞት መድሃኒት ይመስል በከፍተኛ ዋጋ ለሽታ ያህል ነው፡፡… ለወደፊትም የሚመለከተው የንግድ ሚኒስቴር ዓይኑን ወደ ቅመሙ ተራ ዞር እንደሚያደርግ ተስፋ አለን። ካለዚያ ቀስ በቀስ የቅመሙም የዋጋ ጭማሪ እየቀጠለ ሲሄድ፤ ባለሙያዎቹ ካለ ቅመም ወጥ የማይሰሩት የቤት እመቤቶች በአድማ እንዳይነሱና ቅመም የለሽ ወጥ እንዳይመገቡ ነው” በማለት ስጋቷን አጋርታለች፡፡

በዚህች ዓምድ ላይ በዓሉን በማስታከክ ወደ ቀረበው ሌላኛው ጉዳይ እናምራ፤ “የሙያ ድሃ የሆነች የቤት ሰራተኛ ያላቸው ወይዛዝርቶች ገንዘብና ዘንቢል አንጠልጥለው ወደሚያመሩበት የሴቶች ባልትና መደብር ገባን፡፡ በአረንጓዴ በቢጫና በቀይ እንዲሁም ካኪ ቀለም ባለው ወረቀት የታሸገውን ቅመም ቁጥራቸው በዛ ያሉ ወይዛዝርት ሲሸምቱ አገኘን፡፡ …በዚያ ስፍራ ከማቁላሊያው አንስቶ እስከ እርድ የሚገዙትን ሴቶች በተመለከትን ጊዜ፤ በቤቷ ውስጥ ቅመም የምታዘጋጅ ሴት የለችም ብለን ገምተናል።

“ምን ይደረግ ይህም ታስቦ መገዛቱ ታላቅ ነገር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ባል ለጋብቻ የሚፈልገው ሙያና ጠባይ ሳያይ የሚመርጠው ውበትና ሃብት ሆኗል። ታዲያ ማን ቅመም ሲቀምም ይኖራል፡፡ ሀብት ለማጠራቀምና ውበትን ለማሳመር ከአንዱ ሱቅ ወደ አንዱ በመዘዋወር መልክ ማሳመሪያውን መድሃኒት መግዛት እንጂ ጥቁርና ነጭ አዝሙድማ ምን ያደርጋል? ሙያ ፈላጊ በዓል ከሌለ በከንቱ መድከም አያስፈልግም ማለታችን ነው” ስትል መጽሔቷ በጊዜው የነበረውን የባህል መለወጥ በተዘዋዋሪ አጋርታለች፡፡

መቼስ በዚህ ዘመን የሥርዓተ-ጾታ ምልከታ ከታየ ጉዳዩን በሚመለከት  ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በዚያን ዘመን ባል፣ ሚስት ለማግባት የሚያስቀምጠው መስፈርት ምን መልክ እንደነበረው ያስቃኛል፡፡ ከዚህ አንጻር በወቅቱ ሴቷ ተመራጭ እንጂ መራጭ እንዳልነበረች እንዲሁም የቤት ውስጥ ሙያ እንደመስፈርት መቆጠሩ እየደበዘዘ መሄዱን እግረ-መንገዳችንን እንረዳለን፡፡

መነን መጽሔት ቀጠል ታደርግና፣ “…ወይዘሮዋ ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈቀዱም እንጂ ያወሩልን ብዙ ነው። ከነገሩን ውስጥ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በስምንት ሰዓት በኢትዮጵያ ሬድዮ ጣቢያ ‘የምታገቧት ሴት በምን በምን ተሟልታ መገኘት አለባት?’ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወንዶቹ መልስ ሲሰጡ ሙያን አንዳቸውም ሳይጠቅሱ የዳንስ መውደዷንና ጠጉረ ረዥም የሆነችውን መፈለጋቸውን ተናግረዋል” ስትልም አትታለች፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review