
AMN ህዳር 21/2017 ዓ .ም
ቃልን በተግባር መፈጸም የብልጽግና ተጨባጭ መለያዎቹ ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ
የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ አመት የምስረታ በአል የማጠቃለያ መርሀግብር በአደዋ መታሰቢያ ተካሂዷል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት የበአሉ አላማ ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ያደረገውን ጉዞ ለመዘከር እና ቃላችንን ለማደስ ነው ብለዋል።
ፓርቲው በበርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም እነዚህን ፈተናዎች ወደድል በመቀየር አንጸባራቂ ድል ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የትግላችን መዳረሻ ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቃልን በተግባር መፈጸም የብልጽግና ተጨባጭ መለያዎቹ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት አምስት አመታት በሁሉም ዘርፍ የታሪክ እጥፋት የተመዘገበበት መሆኑን አመላክተዋል።
በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ ውጤቶቻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ መናገራቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ አመት የምስረታ በአል “የሀሳብ ልእልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል።
በመርሀግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ እንዲሁም የፓርቲውና የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ።