ቅንጅታዊ አሰራር የአገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት በተጨማሪ ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው-ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ

AMN-ታህሣሥ 9/2017 ዓ.ም

ቅንጅታዊ አሰራር የአገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት በተጨማሪ ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ተናገሩ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ጋር በመሆን በዛሬው ዕለት የፍቺና ጉዲፈቻ የአንድ ማዕከል ምዝገባ ማካሄድ ተጀምሯል።

በመርሐግብሩም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ሴታ እና የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፉአድ ኪያር እንዲሁም የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየውን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በተቋማት ያሉ ቅንጅታዊ አሰራሮች አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ያሉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በተለይ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ከፍርድ ቤቶች ጋር የጀመረው ስምምነት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ስለመሆኑም አንስተዋል።

በፍርድ ቤቶች ከሚሰጡ አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ የተለያዩ ተግባራት የፍርድ ስርዓቱ ላይ ተፅዕኖ እንደነበራቸው ያነሱት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ፉአድ ኪያር ይህ የተቋማቱ የጋራ ስምምነት በፍርድ ቤቶች በሰነድ የተረጋገጠ ማስረጃን በማቅረብ ፍትሃዊ የፍርድ ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የመዲናዋ የሲቪል ምዝገባና እና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የዜጎችን የአገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት በርካታ ስራዎች ስለማከናወኑ የተናገሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ይህም የተረጋገጠና የተደራጀ መረጃ እንዲኖር ስለማስቻሉ አንስተዋል።

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review