በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች እና በአስር የፌደራል ተቋማት የተገነቡ 24 የስማርት ኮሙኒኬሽን ማሳለጫ ክፍሎች በዚህ ሳምንት በይፋ ስራ እንደሚጀምሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከዚህ ቀደም በ5 ተቋማት የተገነቡ ስማርት ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውንም ገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥የስማርት ኮሙኒኬሽን ማሳለጫ ክፍሎቹ የተለያዩ ቦታ ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላትን በቀላሉ እንዲገናኙና ስራቸውን እንዲያሳልጡ የሚያስችሉ ናቸው።
ልዩ ልዩ ስራዎችን፣ስብሰባዎችንና ስልጠናዎችን ጊዜና ወጪን ቆጣቢ በሆነ መንገድ በቀላሉ መምራት የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንደተዘረጋላቸው አመልክተዋል።
ስማርት ስክሪን፣ ስማርት ላይቲንግ፣ የተሻሻሉ የቴሌ እና የቪዲዮ ኮንፈረንሶችን ማድረግ የሚያስችሉ የኔትወርክ፣ የድምፅ ብክለትን የሚቀንሱ(Soundproofing) መሳሪያዎች ተገጥሞላቸዋል ነው ያሉት።
በሀገርአቀፍ ደረጃ 24ቱ የስማርት የኮሙኒኬሽን ክፍሎች ከነገ በስቲያ በተመሳሳይ ሰዓት ተመርቀው በይፋ ስራ እንደሚጀምሩም ገልጸዋል።
በሁሉም ክልሎች፣በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በተመረጡ አስር የፌዴራል ተቋማት የተገነቡት እነዚህ ስማርት የኮሙኒኬሽን ክፍሎች ግንባታ አንድ ዓመት መውሰዱንም ነው የገለጹት።
ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡም ለባለሙያዎች የአጠቃቀም ማንዋልና የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎቹን በሁሉም ተቋማት ለማዳረስ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

See insights and ads
All reactions:
6969