
AMN- ህዳር 4/2017 ዓ.ም
በሁለተኛው ምዕራፍ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን ደረጃ በሚያሻሽል እና ከፍ በሚያደርግ መልኩ 50 የእግረኛ እና መኪና ማቋረጫ ድልድዮች እንደሚገነቡ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ገለፁ።
አቶ ጃንጥራር በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ዙሪያ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም በመግለጫቸው ገልጸዋል።
በኮሪደር ልማቱ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ወጪ ቆጣቢ እና ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የሚሰሩ ዋና ዋና ስራዎች ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ የሚደርስ 21 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዝ ዳርቻው ልማት እንዲሁም 135 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የመንገድ እርዝመት ያለው የአስፋልት መንገድን ያከተተ ነውም ብለዋል።
237 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የልጆች መጫወቻ ቦታዎች ፣79 የሕዝብ መዝናኛ ፣ 111 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የቢስክሌት መንገድ ፣ 114 የመኪና ማቆሚያ እና ተርሚናል ፣ 50 የእግረኛ እና መኪና ማቋረጫ ድልድዮች እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ስራን እንደሚያካትትም ገልጸዋል፡፡
ሰፊ ቁጥር ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ለልማት መነሳቱን እና የቤት አቅርቦትን በማሻሻል እና መሰረተ ልማት በማሟላት እንዲስተናገዱ ተደርጓል ብለዋል።
አብዛኛቹ የልማት ተነሺዎች ማህበራዊ ትስስራቸውን በጠበቀ መልኩ በአንድ አካባቢ እንዲኖሩ መደረጉንም ገልጸዋል።
በዳንኤል መላኩ