
AMN – ታኀሣሥ 10/2017 ዓ.ም
በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ዘላቂ አገልግሎት መስጠትን ታሳቢ ያደረጉ፣ ጥራታቸውን የጠበቁና የከተማዋን አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያልቁ ሆነው እየተገነቡ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ወንድሙ ሴታ ተናገሩ፡፡
ከመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የተገኘውን የተሻለ አፈጸጻም በሁለተኛውም ለመተግበር ስራው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት የጋራ ተግባቦት በመፍጠር ስራው መጀመሩን ኢ/ር ወንድሙ አስታውሰዋል፡፡
በዚሁም መነሻ መሰረተ ልማት ገንቢ ተቋማት ከተማዋን የሚመጥን ደረጃውን የጠበቀ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን በፍጥነትና በጥራት ተቀናጅተው እየገነቡ ይገኛልም ብለዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ እየተዘረጉ ያሉ የመሬት ውስጥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች መዲናዋን የሚመጥኑ፤ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያልቁ እና ነገን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ኢ/ር ወንድሙ አብራርተዋል፡፡
በከተማዋ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በሚከናወኑበት ወቅት ሲያጋጥም የነበረውን የውሃ ብሎም የመብራት መቆራረጥ ያስቀረ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
እለት ተእለት አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች ሳይቋረጡ የእድሳት እና የዝርጋታ ስራ መሰራቱም በኮሪደር ልማቱ የተገኘው ሌላኛው መልካም ተሞክሮ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፍጥነትና በጥራት እየተተገበረ በሚገኘው ይሄው ስራ በትራንስፖርት እንቅስቃሴው ላይ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ የሚያስቀር የተሸከርካሪ ማቆሚያና ተርሚናል ግንባታዎችንም በቅንጅት ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በፍቃዱ መለሰ