ህጋዊ የንግድ ፈቃድን ሽፋን በማድግ ሀሰተኛ ሰነድ ሲያዘጋጅ ያገኘውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት ግለሰቡ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አየር ጤና አካባቢ በሚገኘው ህትመት ቤቱ ልዩ ልዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ እያለ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ/ም እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡
ግለሰቡ ህጋዊ የህትመት ቤትን እንደሽፋን በመጠቀም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች፣ መታወቂያዎች፣ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ፣ የባንክ ደብተር፣ በዋነኝነት የአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የቤተሰብ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት መታወቂያ ሲያዘጋጅ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡
ያዘጋጀዉን ሃሰተኛ ሰነድ ለግለሰቦች ከ400 እስከ 3000 ብር ሲሸጥ እንደነበር በምርመራ መረጋገጡንም የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪውና ግብር አበሮቹ ሀሰተኛ ሰነድ ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸውን ማህተም መቅረጫ ማሽን፣ ላፕቶፕ፣ ፕሪንተሮች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት ማህተሞችና ቲተሮች፣ የአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ የቤተሰብ ነፃ ግልጋሎት መታወቂያ እና የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎችን መያዙንም ጠቅሰዋል፡፡
በወንጀሉ ተጠርጥሮ የተያዘው ግለሰብ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ሲሰራ የነበር እና በስነ-ምግባር ችግር ከተቋሙ መባረሩን ኮማንደር ማርቆስ ጨምረዉ ተናግረዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ