የለውጡ መንግሥት ቀልጣፋ የንግድ ሥርዓትን በመዘርጋት እና አቅርቦት መር የአሰራር ለውጥ በማድረግ የዋጋ ግሽበት ምጣኔን ማሻሻል መቻሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የገቢ እና ወጭ ንግድ እንቅስቃሴ እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የለውጡ አካሄድ በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ትናንትን በጭፍን መመልከት ሳይሆን እዳም ምንዳም አድርጎ የሚረዳ ነው፡፡
በንግዱ ዘርፍም በሀገር ውስጥና በውጭ ንግድ እንዲሁም በጥራት ማረጋገጥ ሂደት የነበሩ ፈተናዎችና እድሎች ተፈትሸዋል ብለዋል፡፡
የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ስህተቶችን ማስተካከልና ጥንካሬዎችን ማዝለቅ የለውጡ መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤የወጭ ንግድ ብዝሃነት እና ተወዳዳሪነትን በማሻሻል ችግር አፈታት ላይ የዳበረ አቅም መገንባት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ የንግድ አመቺነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ላይ የንግድ ሥራ ለመጀመር አመቺ ሁኔታ በመፍጠር በኩል በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን መርካታ አሰራሮች መሻሻላቸውን ጠቅሰው፤በንግድ ፍቃድ አሰጣጥ ሂደትን በማሳጠር ረገድም ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የኦን ላይን የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ስርዓት መተግበሪያ በማበልጸግ ተገልጋዮች ከቤታቸው መስተናገድ የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በሀገራዊ ለውጡ ምቹ የንግድ ከባቢ በመፍጠር ለንግዱ ማህበረሰብ የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ጨምሮ አቅርቦትን ለማሻሻል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በከተማ ግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምርት አቅርቦትን ማሻሻል ተችሏል ብለዋል፡፡
የምርት አቅርቦትን ከማሳደግ ባለፈ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን መቆጣጠር የሚያስችል እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡