AMN – ጥር 16/2017 ዓ.ም
በሊባኖስ እና በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 359 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ እና ለአደጋ የተጋለጡ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር የመመለስ ስራ መቀጠሉን የገለጸው ሚኒስቴሩ በሳምንቱ 156 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ገልጿል።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ከሊባኖስ ወደ ሀገር የተመለሱት 156 ዜጎች 143 ሴቶች 13 ጨቅላ ህፃናት ሲሆኑ ከተመላሾች መካከል 18 እድሜያቸው ከአስራ ስምንት አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ይገኙበታል ነው የተባለው።
በተመሳሳይ በሳምንቱ 185 ወንዶች፣ 15 ሴቶች 3 ጨቅላ ህፃናት በድምሩ 203 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ከተመላሾች መካከል 4 እድሜያቸው ከአስራ ስምንት አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መሆናቸው ታውቋል።
ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ የማድረግ እና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ስራም እየተሰራ እንደሚገኝ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ከሚያዚያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ በሚገኘው ከሳዑዲ ዓረቢያ ዜጎችን የመመለስ ስራ እስካሁን 90 ሺህ 101 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉ ተመላክቷል።