በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

You are currently viewing በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

AMN- መስከረም 30/2017 ዓ.ም

በአሳሳቢ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሊባኖስ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተጠናከረ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በመካከለኛው ምስራቅ በተባባሰው ቀውስ ሳቢያ በስፍራው የሚገኙ ዜጎች ሁኔታ በተመለከተ በከፍተኛ ትኩረት ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ቀውሱ አሁን ከደረሰበት የባሰ ደረጃ ሳይደርስ ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ጭምር በተለይም በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እና የከፋ ስጋት ላይ የሚገኙትንም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተጠናከረ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም እስከትላንት በስቲያ ድረስ በጦርነቱ ተጋላጭ የሆኑ 51 ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏልም ብለዋል።

በስፍራው የሚገኙ ህጋዊም ይሆኑ ሰነድ አልባ ዜጎችን በመለየት ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፤ በአስጊ ሁኔታ ያሉትንም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞነኛ ትኩረት ሆኖ ቀጥሏልም ብለዋል።

በሊባኖስ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች እንደመኖራቸው የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ እየተደረገ ባለው ጥረት በተገኙት የግንኙነት አማራጮች ሁሉ ዜጎችን በመመዝገብ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

እስከ አሁን ባለው መረጃም ከ 3 ሺ በላይ ዜጎች ተመዝግበው አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ማሟላታቸውን አስታውቀዋል።

በቤሩት የሚገኘው የኢፌዴሪ ቆንፅላ ተጨማሪ ሰራተኞችን በመቅጠርም ጭምር ለዜጎች ደህነነት በትጋት እየሰራ መሆኑንም አምባሳደር ነብያት ጠቁመዋል።

በአቡ ቻሌ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review