እኤአ ሰኔ 6 2015 በርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም ፤ በፈገግታ የተሞላች የአምስት ዓመት ልጅ ከአባቷ ጋር ትቦርቃለች፡፡ የባርሰሎና መለያ ቀለም ያረፈበት ባንዲራ ዘንግ ትወዘውዛለች፡፡
ዘንጉ ከአቅሟ በላይ ቢሆንም ደስታው ይህን እንድታስተውል አላደረጋትም፡፡ በአሰልጣኝነት ዘመኑ የመጀመሪያ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ያነሳው አባቷ በመደነቅ ያያታል፡፡
ደስታዋ ልዩ ስለነበር ፤ እርሱም አብሯት ይፍነከነካል፡፡ ይህቺ ህፃን ዣና የሚል ስም ነበራት፡፡ የተወለደችው እኤአ 2009 ላይ ነበር፡፡ የሊውስ ኤነሪኬ የመጨረሻ ልጅም ነበረች፡፡ ገና 10 ዓመት እንኳን ሳይሞላት 2019 ላይ አጣት እንጂ፡፡
ዣና ’’ኦስቴኦሳርኮማ’’ የተሰኘ የአጥንት ካንሰር ሲያዛት ገና 9 ዓመቷ ነበር፡፡ ለአራት ወር በሆስፒታል ተኝታ ህክምናዋን ተከታተለች፡፡
ከህመሟ ልትፈወስ ግን አልቻለችም፡፡ ሊውስ ኤነሪኬ በወቅቱ የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነበር፡፡ የመጨረሻ ልጁ ህመም የከፋ መሆኑን ሲያውቅ ስራውን አቆመ፡፡
አምስት ዓመቷ ላይ እያለች የቻምፒየንስ ሊግ ድሉን አብሯት ያጣጣመው ልጁ እንደማትተርፍ አወቀ፡፡ ያቺ የሚሳሳላት ፤ ሁሌም የደስታ ምንጩ የሆነችው ልጅ ከእቅፉ ልትወጣ ነው፡፡ አምኖ ለመቀበል ቢቸገርም አማራጭ የለውም፡፡
እራሱን ማጠንከር አለበት፡፡ ስፔናዊ አሰልጣኝም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ ከልጁ ጋር ያሳለፋቸው ጣፋጭ 9 ዓመታት ብርታት ሆነውት ወደ ስራ ለመመለስ ወሰነ፡፡
’’በሕይወትህ የሚገጥሙህ ቅስም ሰባሪ አጋጣሚዎች ትልቅ አስተማሪ ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ልጅህን በ9 ዓመቷ አጥተሃት ይሉኛል፡፡ ልጄ ከእኔ ጋር ድንቅ 9 ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ በሺ የሚቆጠሩ የእርሷ ትውስታዎች አሉኝ፡፡ ሰዎች እንደ እድለቢስ ሊያዩኝ ይችላሉ ፤ አይደለም እኔ እራሴን በጣም እድለኛ አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡’’ ሲል ስለእርሱ በተሰራ ዘጋቢ ፊልም ላይ ገልፆ ነበር፡፡
ሊውስ ኤነሪኬ ዣናን ካጣ 6 ዓመት በኋላ ፓሪሰን ዠርማ እየመራ ለአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ደርሷል፡፡ የ55 ዓመቱ አሰልጣኝ ልጄ ሁሌም በመንፈስ ከእኔ ጋር ናት ይላል፡፡
የበለጠ ብርታት የማገኘውም ከጎኔ እንደሆነች ሳስብ ነው፡፡ የበለጠ ስኬት የምመኘውም ለእርሷ ነው ይላል፡፡ የፊታችን ቅዳሜ ፓሪሰን ዠርማ እየመራ ኢንተር ሚላንን አሸንፎ ዋንጫ ካነሳ መታሰቢያነቱ በስራው የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ላደረገችው ልጁ ይሆናል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት በበርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም ከልጁ ጋር እየቦረቀ የቻምፒየንስ ሊግ ድሉን አጣጥሟል፡፡ አሁን ደግሞ በመንፈስ ካልተለየቸው ልጁ ጋር የዋንጫ ድሉን ማክበር ይፈልጋል፡፡ በርካታ ይህን ታሪክ የሰሙ የስፖርት ቤተሰቦችም እንዲሳካለት ተመኝተውለታል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ