በሎስ አንጀለስ በተከሰተው ሰደድ እሳት እስካሁን የ24 ሰዎች ሕይወት አልፏል

You are currently viewing በሎስ አንጀለስ በተከሰተው ሰደድ እሳት እስካሁን የ24 ሰዎች ሕይወት አልፏል

AMN – ጥር 5/2017 ዓ.ም

ከቀናት በፊት የሎስ አንጀለስ ባለሥልጣናት ሰደድ እሳቱ በቁጥጥር ሥር መዋሉን እና ነዋሪዎችም ከአካባቢያቸው እንዲወጡ የተላለፈው ውሳኔ መነሣቱን አስታውቀው ነበር።

ሆኖም በከባድ ንፋስ ምክንያት ሰደድ እሳቱ ዳግም አንሰራርቶ በሰው ልጅ ሕይወት እና በንብረት ላይ ውድመት ማድረሱን ቀጥሏል።

በአደጋው እስካሁን 24 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ስምንቱ በምዕራቡ የከተማዋ ክፍል በተከሰተው ‘ፓሊሴድ’ ተብሎ በሚጠራው የሰደድ እሳት ምክንያት የሞቱ ናቸው።

16ቱ ደግሞ በምሥራቅ ሎስ አንጀለስ በደረሰው ኢቶን በተባለው ሰደድ እሳት ነው የሞቱት።

የ‘ፓሊሴድ’ ሰደድ እሳት እጅግ ግዙፉ ሲሆን እስካሁን ድረስም ከ9 ሺህ 307 በላይ ሔክታር መሬት ላይ ተዛምቷል። ከዚህ ውስጥም 13 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው መቆጣጠር የተቻለው።

ሁለተኛው ግዙፉ ሰደድ እሳት ‘ኢቶን’ የተሰኘው ሲሆን ከ5 ሺህ 665 ሔክታር በላይ መሬት ላይ ተስፋፍቷል። 27 በመቶ ያህሉን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉ ነው የተገለጸው።

ከ323 ሔክታር በላይ መሬት ላይ ተዛምቶ ጉዳት ያደረሰው እና 3ኛ ደረጃን የያዘው ደግሞ በሰሜን የከተማዋ ክፍል የተከሰተው ‘ሀርስት’ የተሰኘው ሰደድ እሳት ነው። ይህ ሰደድ እሳት 89 በመቶ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አልጀዚራ ዘግቧል።

እስካሁን በኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው የጉዳት መጠን ከ250 እስከ 275 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል።

ከአደጋው ጋር ተያይዞ ዜጎች ከመኖሪያቸው መውጠታቸውን ተከትሎ 29 የሚሆኑ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ የእሳት አደጋ መከላከል ሠራተኛ መስልው መኖሪያ ቤቶችን ሊዘርፉ ሲሉ በፖሊስ ተይዘዋል።

የሎስ አንጀለስ አስተዳደር በአካባቢው የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ቀድመው ከገቡት 400 የብሔራዊ ዘቦች በተጨማሪ ሌሎች 1 ሺህ የሚሆኑ የፀጥታ አካላት በአካባባው ይሰፍራሉ ብሏል።

በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ካሊፎርኒያ 14 ሺህ የእሳት አደጋ መከላከል ሠራተኞች በ1 ሺህ 354 አውሮፕላኖች ታግዘው ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ።

የካሊፎርኒያው አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም የሰደድ እሳቱ ካደረሰው ጉዳት አንጻር በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእሳቱ የመስፋፋት ባህሪ አንጻር 10 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት የሎስ አንጀለስ ከተማ ከፍተኛ ስጋት ተጋርጦባታል።

የከተማዋ ባለሥልጣናት በትናንትው ዕለት ብቻ 100 ሺህ ሰዎች ከቀዬአቸው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ሌሎች ተጨማሪ 87 ሺህ ነዋሪዎችም ቀዬአቸውን ለመልቀቅ ሊገደዱ ይችላሉ ተብሏል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በአካባቢው ስለተከሰተው የሰደድ እሳት ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን ሊደረግ ስለሚገባው ድጋፍም መረጃ አግኝተዋል።

ከ7 ቀናት በኋላ በዓለ ሲመታቸውን የሚያደርጉት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰደድ እሳቱን አስመልክተው ባለሥልጣናቱ ላይ ትችት መሰንዘራቸው የሚታወስ ነው።

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review