በሎስ አንጄለስ ለተቃውሞ የወጡ ሰነድ አልባ ስደተኞች የፈጠሩትን አለመረጋጋት ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወታደሮችን በስፍራዉ አሰማርተዋል፡፡
ሶስተኛ ቀኑን በመያዘዉ በዚህ ተቃዉሞ ሠልፈኞቹ ከፌደራል የስደተኞች እና የጉሙሩክ ፖሊሶች ጋር መጋጨታቸዉ ተጠቁሟል፡፡
ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከግዛቲቱ ለማስወጣት በተወሰደ እርምጃ ከ118 ሰዎች በላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸዉ ነዉ የተዘገበዉ፡፡
የኤፍቢአይ ምክትል ዳይሬክተር ዳን ቦንጊኖ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ እንዳስታወቁት ህገ መንግስቱን ለማስከበር የማንም ፍቃድ አያስፈልገንም ብለዋል፡፡
ተቃዋሚዎቹ ለህግ የማይገዙ ከሆነ እርምጃ በመዉሰድ ሕግ እና ስርዓት እናሰፍናለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በአሁኑ ሰአት ሎስአንጀለስ በከባድ ወንጀለኞች ተጥለቅልቃለች ህግ እና ስርዓትን እናስከብራለን ማለታቸውንም አልጄዚራ በዘገባው አስነብቧል።
የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ግጭቱ ወደሌሎች ከተሞች እንዳይዛመት 2ሺህ የብሄራዊ ዘብ ጠባቂዎችን በስፍራው ማሰማራታቸውም ተገልጿል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ