“ በሕግና በሥርዓት የሚመራ፣ የሰዎች መብት የማይጣስበት የወንጀል ምርመራ ሥርዓት ተዘርግቷል” – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

You are currently viewing “ በሕግና በሥርዓት የሚመራ፣ የሰዎች መብት የማይጣስበት የወንጀል ምርመራ ሥርዓት ተዘርግቷል” – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

AMN – መጋቢት 10/2017 ዓ.ም

አሁን ላይ በሕግና በሥርዓት የሚመራ፣ የሰዎች መብት የማይጣስበት የወንጀል ምርመራ ሥርዓት መዘርጋቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በነፃነት ሥራውን የሚሠራበት፣ ምንም አይነት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የሌለበት፣ ለሁሉም አካላት እኩል ለማገልገል ጥረት የሚደረግበት ተቋም ሆኖ እንደሚሰራ የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራሉ፣ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የጠበቀ ማህበረሰብ አቀፍ እና መረጃ መር የወንጀል መከላከል ሞዴል እና ማስረጃና መረጃ መር የወንጀል ምርመራ መርህን እየተከተለ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ፖሊስ ሕግና የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር ነፃ ሆኖ ከተደራጀ የማደግ ዕድሉ በጣም ሰፊ ነው ያሉት ኮሚሸነር ጀነራሉ፣ ከተቋማዊ ሪፎርም በፊት ፖሊስ ከነበሩ ሥርዓቶችና የፖለቲካ ሂደቶች ጋር የተቆራኘ ስለነበር በዕድሜው ልክ ሀገራችን በምትፈልግበት የዕድገት ደረጃ ላይ ሳይደርስ መቆየቱንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ከሪፎርም በፊት የሕዝብ አመኔታን ያጣ፣ እንደ ሀገርና በተቋሙ ውስጥ አለመረጋጋት እና የብቃት ችግር በስፋት ሲስተዋልበት እንደነበር የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ ጠንካራ የፖሊስ ተቋም ሊኖረው ስለሚገባ የሪፎርም ሥራ እንዲተገበር መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሊፈጸሙ የነበሩ የሽብር ተግባራትና የተደራጁ ወንጀሎችን አስቀድሞ በማክሸፍ እና የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ጨምሮ ሌሎች ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን ሰላምና ደህንነት በማስከበር ኢትዮጵያ ጠንካራ የፀጥታ ተቋም እንዳላት አሳይቷል ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራሉ።

በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ኤርፖርቶችን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በሀገራችን የፖሊስ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ዘመናዊ የሞተር ጀልባዎችን በመታጠቅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በመሰማራት የሚሠራ የኮስታል ጋርድ ፖሊስ ዲፓርትመንት መቋቋሙን እና በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ኮሚሽነር ጀነራሉ መግለፃቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review