AMN – ጥር 14/2017 ዓ.ም
በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሚታዩ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የተጀመሩ የሪፎርም ትግበራና የዝግጅት ሥራዎች አበረታች ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አመራር ዐቢይ ኮሚቴ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂደናል ብለዋል።
በውይይታችን በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና በመጀመሪያ ዙር የተመረጡ ተቋማት ያከናወኗቸውን የሪፎርም ሥራዎች ገምግመናል ሲሉ ገልጸዋል።
የሪፎርም አስተዳደራዊ ሥራዎች፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓትን መዘርጋት፣ የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት አገልግሎቶችንና ውሳኔዎችን ማቀላጠፍ ላይ ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውንም ተመልክተናል ብለዋል።
በሪፎርሙ የታቀፉ ተቋማትም ያላቸውን ልምዶች የሚቀያየሩበት እና ተቀራርበው የሚሰሩበትን አውድ መፍጠር ተችሏል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
ተቋማት ያከናወኗቸውን ተግባራት በዝርዝር በመቃኘት ጥንካሬዎችንን ውስንነቶችን የለየን ሲሆን በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ላይም አቅጣጫ አስቀምጠናል ሲሉም አመልክተዋል::