የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት እና ለተጠሪ ተቋማት የመስክ ምልከታ ግብረ መልስ ሰጥቷል።
በመዲናዋ እየተገነቡ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የቀጣዩን ትውልድ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን በመስክ ምልከታ ማረጋገጥ መቻሉን የመሰረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ግዛቸው አይካ ገልጸዋል፡፡
በኮሪደር በለሙ የመንገድ ዳርቻዎች እና የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ዳር መብራቶች ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባም ሰብሳቢው ገልጸዋል።
መጪው ጊዜ ክረምት እንደመሆኑ መጠን የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት የቅድመ መከላከል ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበትም ተመላክቷል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፣ የቋሚ ኮሚቴው ግብረ መልስ ተጨማሪ አቅም የሚሰጥ እና የማህበረሰባችን ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ የተደረገባቸው ተቋማትም የአዲስ አበባ የእሳት አደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና ቅርንጫፍ ጣቢያዎች ፣ የሲቪል እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ እና በስሩ የሚገኙ የተወሰኑ ወረዳዎች፣ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ እና የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
በዳንኤል መላኩ