በመዲናዋ ለተገኘው አስተማማኝ ሰላም ሕዝባዊ የሰላም አደረጃጀት ሚናው ከፍተኛ ነው ተባለ

AMN – ግንቦት 2/2017

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና የወሰዱ አሥራ አንድ ሺ 4ኛ ዙር የሰላም ሰራዊት አባላትን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አስመርቋል።

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ በመዲናዋ አሁን ለተገኘው አስተማማኝ ሰላም ሕዝባዊ የሰላም አደረጃጀት ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ፍጥነት እየለማች እና እየተለወጠች በመሆኑ ህዝቡ ሰላሙን በባለቤትነት ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፣አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት እና የሰላም ደሴት ለማድረግ በሚከናወን ተግባር ውስጥ ነዋሪው እና የሰላም ሰራዊት አባላት ከጸጥታ መዋቅር ጋር በመሆን ከፍተኛ አብርክቶ አድርጓል ብለዋል።

አሁንም ከጸጥታ መዋቅር እና ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት የአዲስ አበባ ከተማን አስተማማኝ ሰላም በማስቀጠል ሂደት የሰላም ሰራዊት አባላት ከፍተኛ ሚና አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ጨምሮ የከተማ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች በምረቃ መርሃግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

በዳንኤል መላኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review