AMN-የካቲት 27/2017 ዓ.ም
በመዲናዋ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እና ህገወጥ ተግባራትን ለመግታት የማይታይ፣ የታጠፈ እና የተደመሰሰ ሰሌዳን ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እና ህጋዊ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ከኤ ኤም ኤን ውሎ አዲስ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሙያና ህዝብ ግንዛቤ ዲቪዝን ሃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ፣ አሽከርካሪዎች ህጎችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራቱን እና አሁን ላይ ተጨባጭ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ግንዛቤ የመፍጠር እና አጥፊዎችን ተጠያቂ የማድረግ ስራው በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ኢንስፔክተር ሰለሞን ፣ ከየካቲት 16 እስከ የካቲት 28 ብቻ ከ 1 ሺ 500 በላይ ተሸከርካሪዎች እና አሽከርካሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
እየተወሰደ ያለው ርምጃ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርስ ሞትን እና የንብረት ውድመትን የሚያስቀር ነው ብለዋል፡፡ የቁጥጥር ስራው በሁሉም አካላት ላይ ተግባራዊ የሚሆንና ህጋዊ ሆኖ መንቀሳቀስን እውን የሚያደርግ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
የማይታይ፣ የታጠፈ እና የተደመሰሰ ሰሌዳን አድርገው የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለሌብነት እና ማጭበርበር መነሻ እየሆኑ ነው ያሉት ኢንስፔክተር ሰለሞን ፖሊስ መሰል የደንብ ጥሰት በሚፈጽሙ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር እና ርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ኃላፊው አሽከርካሪዎች ህግን አክብረው እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተመስገን ይመር