በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የከተማው መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ ተናግረዋል፡፡
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የመምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ፤ ትውልድን በመቅረጽ ትልቅ ሚና ካላቸው ሙያዎች መካከል የተከበረው የመምህርነት ሙያ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የእዚህ ሙያ ባለቤት የሆኑት መምህራንም ከመኖሪያ ቤት ጋር ተያይዞ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ነበሩ ያሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አስተዳደሩ የመምህራኑን ጥያቄ በመቀበል ውጤታማ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የመምህራንን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ ከእነዚህ ስራዎች መካከልም መምህራን የነጻ ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ትውልድን በስነ ምግባርና እውቀት ቀራጭ የሆኑት የአገር ባለውለታ መምህራን የጤና እክል በሚገጥማቸው ወቅት የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሆስፒታልን ለመገንባት የሚያስችል ከሊዝ ነጻ የመሬት አቅርቦት ከተማ አስተዳደሩ አድርጓል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ አስተዳደሩ ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚውል የ50 ሚልዮን ብር ድጋፍ እንዳደረገላቸውም ገልጸዋል፡፡
በየሺዋስ ዋለ