
AMN – ኅዳር 10/2017 ዓ.ም
በመዲናዋ በሁሉም ዘርፎች በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን የምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክርቤት 4ተኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በሚገኘው የምክርቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
በጉባኤው የምክር ቤት አባላት በቋሚ ኮሚቴዎቻቸው የቀረቡ አስተያየቶች እና ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት በከተማዋ በሁሉም ዘርፎች በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ አዲስ አበባ ከ123 ከተሞችና 72 ሀገራት ጋር በመወዳደር በስማርት ሲቲ ሊደርሺፕ እውቅና ማግኘቷ ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህም የከተማ አስተዳደሩ የትኩረት አቅጣጫ የሆነው የስማርት ሲቲ ግንባታ እውን እየሆነ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምቹ የስራ አካባቢን ለመፍጠር የከተማ አስተዳደሩ መስሪያ ቤቶችን ስማርት ለማድረግ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ እና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም አገልግሎት አሰጣጡን ከብልሹ አሰራርና ሌብነት ለማጽዳት የተጀመረው በኦንላይን አገልግሎት የመስጠት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በከተማዋ ገበያን ለማረጋጋት ትልቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የምክር ቤት አባላት በተለይ በገበያ ማዕከላትና በእሁድ ገበያዎች ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት አይነተኛ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ከመጀመርያው ዙር በተሻለ የአመራር ቁርጠኝነት በማይታመን ፍጥነት ውጤት እየታየበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በልማት ስራዎች ላይ እየታየ ያለው መሻሻል አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ደረጃዋን ለማስጠበቅ እንደሚያግዛት ተመላክቷል፡፡
ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚኖሩ ሴቶችን ለመደገፍ የተቋቋመው “የነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሴቶችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አስመርቆ ስራ ማስጀመሩ የሚበረታታ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የምክር ቤት አባላቱ አሳስበዋል፡፡