AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመዲናዋ በህክምና ማዳን የማይቻሉ ህመሞች የሚያደርሱትን ስቃይ መቀነስ ላይ እተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡
ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ፣ ከዚህ ቀደም የጤናው ፖሊሲ የመከላከል እና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁንና አሁን ላይ ታክመው መዳን ለማይችሉ ሰዎች ሥቃያቸውን ማስታገስ እና ከህመም ስሜት ነፃ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
96 ጤና ጣቢያዎች እና 6 ሆስፒታሎች የሚገኙባት አዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ታክሞ መዳን የማይችል ህመም ያለባቸው ሰዎች አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዳልነበር የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ሃላፊው፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን አገልግሎቱ በ14 ጤና ጣቢያዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
ጤና ጣቢያዎቹ አገልግሎቱን እየሰጡ የሚገኙት ከሆስፒታሎች ጋር በተሰራ የማስተሳሰር ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አንድ ሰው ካንሰር ቢታመም እና ህመሙ በጨረርም ሆነ በመድሃኒት መታከም የማይችል ከሆነ እንዲሁም ህመም ካለው ማስታገሻ ለማግኘት የግድ ትልልቅ ሆስፒታሎች መሄድ ሳያስፈልገው መድሃኒቶችን ከጤና ጣቢያ ማግኘት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
እንደ አጠቃላይ በጤና ሥርዓቱ ላይ በእያንዳንዱ ክፍል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝም ምክትል ቢሮ ሃላፊው አብራርተዋል፡፡
በታምራት ቢሻው