
AMN – ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 47 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
ቢሮው በ2017 የመጀመሪያ ሩብ አመት በትስስር ከፌዴራል፣ ከአዲስ አበባ እና ከክልል ተቋማት ጋር በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ላይ የግምገማ መድረክ አካሂዷል።
በመጀመሪያው ሩብ አመት ከተለያዩ ዘርፎች 47 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን የተናገሩት የቢሮው የሞደርናይዜሽንና ኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አዳነ ሱሌ፣ በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ለልማት የሚያውለውን ገቢ ለመሰብሰብ ከፌዴራልና ክልል እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ጋር የተጠናከረ ስራ ይሰራል ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ውቀት ጋር ሲነጻጸርም የ10 ቢሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱን በመግለጽ በዚህም የዕቅዱን 83 ነጥብ 9 ከመቶ አፈጻጸም ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይም ቢሮው በ2017 ዓ .ም የ230 ቢሊየን ብር ገቢ የመሰብሰብ ዕቅዱን ለማሳካት ከፌዴራልና ከክልል ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ምክትል ቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል።
በዓለሙ ኢላላ