በመዲናዋ በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ የወንጀል ምጣኔ እና የደንብ ጥሰቶች መቀነሳቸውን የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ሰላምና አስተዳደር ቢሮ እና ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የበጀት ዓመቱን 9ወራት እቅድ አፈጻጸም እየገመገሙ ነው።
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ የወንጀል ምጣኔ እና ህገወጥ ተግባራት እንዲቀንሱ ሆነዋል።
ህዝቡን ያሳተፈ የጸጥታ አደረጃጀት እንዲኖር በማድረግም ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ስለመደረጉም አንስተዋል።
የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች እና ሌሎች ተግባራት በየአካባቢው እንዲከስሙ ከማድረግ አንጻር የሰላም ሰራዊት የማይተካ ሚና እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
በከተማዋ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሰላም ሰራዊቱ ሚናውን እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።
በዚህም የሰላም ሰራዊትን በሰው ሀይል ለማደራጀት ያስችል ዘንድ በቅርቡ ከ33ሺህ በላይ የሰላም ሰራዊት አባላት ሰልጥነው እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ በተሰራው ስራ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውር እና ወንጀል ፈጻሚ ጸጉረ ልውጦችንም መከላከል መቻሉን አንስተዋል።
በሄለን ጀንበሬ