AMN-ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ በ2017 ክረምት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ የአረንጓዴ ሽፋን ከሶስት በመቶ ያልበለጠ እንደነበረ በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል፡፡
ይህንንም ለመለወጥ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰሩ ተከታታይ የአረንጓዴ አሻራ ክንውኖችም የደን ሽፋን ከሃያ በመቶ በላይ መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከ85 ሚሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል ብለዋል፡፡
በ2017 ክረምት በከተማ ደረጃ ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከ78 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ምዕራፍ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለከተማው የአረንጓዴ ሽፋን ዕድገት የበኩሉን ሚና አበርክቷል ያሉት የቢሮ ሃላፊው፤ የወንዝ ዳርቻ ልማትን ጨምሮ በቀጣይ የከተማውን የአረንጓዴ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዓለሙ ኢላላ