በመዲናዋ ባለፉት አምስት አመታት የተሰሩ የልማት ስራዎች የሚዳሰሱ እና በተጨባጭ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-ኃዳር 12/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት አምስት አመታት የተሰሩ የልማት ስራዎች የሚዳሰሱ እና በተጨባጭ የሚታዩ እንዲሁም የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና በብልጽግና መርህ መሠረት አካታች የሆኑ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘውን 5ኛ ዓመት የብልጽግና ፓርቲ ምስረታን በዓልን በማስመልከት ባለፉት አምስት አመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ ተግባራትን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በመስቀል አደባባይ ተከፍቷል።

ብልጽግና ፓርቲ በሀሳብ ተወልዶ በሀሳብ ልዕልና ተወዳድሮ እና በህዝብ ተመርጦ መንግስት ሆኗል ያሉት አውደ ርዕዩን የከፈቱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በብልጽግና ፓርቲ ሀሳብ ትልቅ ስፍራ አለው ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ያሉት ከንቲባ አዳነች በአዲስ አበባ ከተማም ይህ መረጋገጡን ገልጸዋል።

እነዚህ ስኬታማ ስራዎች ሲሰሩ መንገዶች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነው አይደለም ያሉት ከንቲባዋ በሀሳብ ልዕልና የማይምኑ ሀይሎች የኢትዮጵን የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍና ወደ ኋላ ለመመለስ መጣራቸውን ተናግረዋል ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ለሁለንተናዊ ብልጽግናዋ የሚጠቅም ሀሳብ እንጂ ጦርነት አይደለም ብለዋል።

ባለፉት አምስት አመታት በአዲስ አበባ ከተማ በብልጽግና የሰው ተኮርነት መርሆ ላይ ተመስርተው የተሰሩ የልማት ስራዎች ከተማዋን እንደስሟ አዲስና አበባ እንዲሁም ለኑሮ ምቹ ያደረጉ የነዋሪውንም ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናግረዋል።

በመስቀል አደባባይ የተከፈተው አውደ ርዕይ ለቀጣይ ሶስት ቀናት ክፍት ሆኖ ይቆያል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review