በመዲናዋ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ እና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን መንገዶች ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing በመዲናዋ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ እና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን መንገዶች ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

AMN – ሚያዚያ 22/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሄዷል፡፡

የምክር ቤት አባላትም ከህዝብ የተሰበሰቡ ጥያቄዎችን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም ከአመታት በፊት በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ተጀምረው ያልተጠናቀቁና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ጥገና ሁኔታ በተመለከተ ይገኙበታል፡፡

ለቀረቡት ጥያቄዎችም የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙህዲን ረሻድ (ኢ/ር) ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመዲናዋ ከአመታት በፊት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ መንገዶችን ለማጠናቀቅ እና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለመጠገን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ተጀምረው እስካሁን ያልተጠናቀቁ መንገዶች በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት እንደነበር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣አሁን ላይ ከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ችግሩ ተፈትቶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

ስራውን በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ጥገና በተመለከተም በየቦታው የሚሰሩ ስራዎች በርካታ በመሆናቸው፣ ቅድሚያ ለዋና ዋና መንገዶች መስጠት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችንም በተያዘላቸው ጊዜ መሰረት ለማከናወን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የዋና ዋና መንገዶችን ጥገና በአብዛኛው የተከናወነ በመሆኑ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን የመጠገኑ ስራ ተጀምሯል፤ ይህንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review