በመዲናዋ እየተካሔዱ ያሉ የልማት ሥራዎች የከተማ አስተዳደሩ በጀት በትክክል ልማት ላይ ለመዋሉ ማሳያ ናቸው- የምክር ቤት አባላት

You are currently viewing በመዲናዋ እየተካሔዱ ያሉ የልማት ሥራዎች የከተማ አስተዳደሩ በጀት በትክክል ልማት ላይ ለመዋሉ ማሳያ ናቸው- የምክር ቤት አባላት

AMN-የካቲት 10/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄዱ እና እየተካሔዱ ያሉ የልማት ሥራዎች የከተማ አስተዳደር በጀት በትክክል ልማት ላይ ለመዋሉ ማሳያ መሆናቸውን የከተማዋ የምክር ቤት አባላት ገለፁ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ እስካሁን ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁ መሠረተ ልማቶችን እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ጉብኝቱ የልማት ስራዎችን በተያዘለት በጀትና ዕቅድ መሠረት እያከናወነ መሆኑን ለመገምገም እና በቀጣይም ድጋፍና ክትትልን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል ነው ተብሏል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የመዲናዋን ገፅታ የቀየሩ፣ ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ፣ የሥራና የመዝናኛ አካባቢን የፈጠሩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በርካታ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የመንገድ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የመልሶ ግንባታ፣ የመዝናኛ ፓርኮችና ሌሎችም የአገልግሎት ማዕከላትን ያካተተ የኮሪደር ልማት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለፁት፤ ምክር ቤቱ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን በጀት ለልማት ሥራዎች እንደሚመድብ እና በጀቱም ለልማት መዋሉን ክትትል እና ቁጥጥር እንዲሁም ለአፈጻጸሙም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን የልማት ሥራዎች በተጨባጭ ለማየት ምክር ቤቱ የመስክ ምልከታ አከናውኗል ነው ያሉት።

ከጉብኝቱ በኋላ የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ፣ምክር ቤቱ ያፀደቀው የልማት በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች እና በኮሪደር ልማቱ የተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ መሆናቸውን በመግለፅ ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት የህብረተሰቡን ቀና ትብብር አድንቀዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ በካዛንቺስ አካባቢ ባደረጉት የኮሪደር ልማት ጉብኝት የልማቱ መፋጠን ለከተማዋ ድምቀትን እንደፈጠረም ተናግረዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review