በመዲናዋ የመንጃ ፈቃድ ዕድሳት አገልግሎት በመታወቂያ አድራሻ ሳይገደብ በየአቅራቢያው እንዲሰጥ ተፈቀደ

You are currently viewing በመዲናዋ የመንጃ ፈቃድ ዕድሳት አገልግሎት በመታወቂያ አድራሻ ሳይገደብ በየአቅራቢያው እንዲሰጥ ተፈቀደ

AMN-መጋቢት 23/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ከመጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የመንጃ ፈቃድ ዕድሳት አገልግሎት በመታወቂያ አድራሻ ሳይገደብ በየአቅራቢያው እንዲሰጥ ተፈቅዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 84/2016 የተዋቀረው የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በሁለት ዘርፍ ከ55 በላይ ዋና ዋና አገልግሎቶችን ይሰጣል።

በዚህ አግባብ የአሽከርካሪ ዘርፍ ከተሰጠው ሥልጣን እና ተግባር ውስጥ ብቁ አሽከርካሪ ማፍራት ዋናው ተልዕኮው ነው።

ተቋማሙ በሪፎርም ሂደት ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ፣ ህዝቡ በዘርፉ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ በርካታ አሰራሮችን በማሻሻል የተገልጋይ ዕርካታን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እና ለውጥ እየተደረገ ነው።

በ2017 በጀት ዓመት ከተለዩ ለዓመታት የከረሙ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ በመታወቂያ አድራሻ ሳይገደብ በአቅራቢያ መንጃ ፈቃድ የማደስ ጥያቄ ይገኝበታል።

በተቋሙ የአሽከርካሪ አገልግሎት የሚሰጥበት ሲስተም የተማከለና አስተማማኝ እንዲሆን ቀድሞ ሰፋፊ የማሻሻያ ተግባራት መሰራታቸውን ማረጋገጥ መቻሉ ተገልጿል፡፡

በዚህም የተቋሙ ስትራቴጅክ ማኔጅመንት ከመጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተገልጋዮች በሚቀርባቸው ቅርንጫፍ ፋይላቸው ያለበት ቅርንጫፍ ሳይጠየቅ የጤና ምርመራ ሰርተፍኬትን በመያዝ የመንጃ ፈቃድ ዕድሳት አገልግሎት እንዲያገኙ መወሰኑ ተመላክቷል።

በቀጣይም ተቋሙ በዘርፉ የተገልጋይ ዕርካታ በመጨመር፣ የህዝብ አመኔታ የሚጣልበት እስኪሆን ድረስ በትጋት የሚሰራ መሆኑን መግለጹን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review