AMN-ጥር 18 /2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የጤና ተቋማትን አገልግሎት በማዘመን የእናቶችና ህፃናትን ሞት መቀነስ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሀንስ ጫላ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዘመናዊ የጤና ስርዓት ለመገንባት ነባር ሆስፒሎችን የማዘመን እና አዳዲስ የጤና ተቋማት የመገንባት ስራ ተሰርቷል፡፡
የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶችን በማሳደግ በሽታ የመከላከልና የማከም አቅምን በማጎልበት የነዋሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት በትጋት መሰራቱን ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡
በተለይም የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በ2013 ዓ.ም ስራ የጀመረው አበበች ጎበና መታሰቢያ የእናቶችና የህጻናት ሆስፒታል እጅግ ዘመናዊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በተጨማሪም ከቅርብ ዓመታት በፊት በአንድ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ የነበረው እናቶችን በኦፕሬሽን የማዋለድ አገልግሎት ዛሬ ላይ በ19 ጤና ጣቢያዎችና በተለያዩ ሆስፒታሎች እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
በአንዲት ሀገር ውስጥ ለመውለድ ሆስፒታል ከገቡ መቶ ሺ እናቶች መካከል የሚሞቱ እናቶች ቁጥር በ2030 ከ70 ማነስ እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሃሳብ ያመላክታል፡፡
አዲስ አበባም በዚህ ስርዓት ስትመዘን በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ዶክተር ዮሃንስ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ ዘመናዊ የጤና ስርዓት ለመዘርጋት በተከናወኑ በርካታ ስራዎችም ሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች እና 51 ጤና ጣቢዎች ከወረቀት ነፃ አገልግሎት በመስጠት ታካሚዎች ካርድ ለማውጣት የሚባያባክኑትን ጊዜና ጉልበት ማስቀረት መቻሉ ተመላክቷል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች እያንዳንዳቸው 450 አልጋ የሚይዙ ዘመናዊ ሆስፒታሎች ግንባታቸው በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን 30 የጤና ተቋማትም ማስፋፍያ እንደተደረገላቸው ዶክተር ዮሃንስ ተናግረዋል፡፡