በመዲናዋ የጥምቀት ክብረ በዓል አምስት ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ተግባራት ይሰማራሉ:- ማኅበሩ

You are currently viewing በመዲናዋ የጥምቀት ክብረ በዓል አምስት ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ተግባራት ይሰማራሉ:- ማኅበሩ

AMN – ጥር 7/2017 ዓ.ም

የጥምቀት ክብረ በዓል በድምቀት እንዲከበር አምስት ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ለማሰማራት ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታወቀ፡፡

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ ደምቆ የሚከወነው ጥምቀት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)) የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከአያሌ አድባራት የሚወጡ ታቦታት በተለያዩ ስፍራዎች በአንድ ስፋራ በሚያድሩበት እና ዕልፍ አዕላፍ ምዕመናን በሚታደሙበት በዚህ በዓል ታዲያ የበጎ ፈቃድ ወጣቶች ሚና አይተኬ ነው።

ታቦታት ባሕረ ጥምቀት አድረው እስኪመለሱ ድረስ በዓሉ ኀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀትና በሰላም እንዲከበር ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰማራሉ።

በአዲስ አበባ ለሚከበረው የጥምቀት በዓል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ የወጣት አደረጃጀቶች መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ነው።

የማኅበሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የተመኝ አስማማው እንዳለችው፤ ማህበሩ ጥምቀት ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር በየዓመቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያከናውናል።

በዘንድሮ ክብረ በዓልም በማስተባበር፣ በጽዳትና በሌሎች የበጎ ፈቃድ ተግባራት ለሚሰማሩ ወጣቶቹ ከወዲሁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል ብላለች።

በዚህም የጥምቀት የአደባባይ በዓል በድምቀትና በሰላም እንዲከበር ከጸጥታና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የበኩሉን ሚና ለመወጣት በቂ ዝግጅት ማጠናቀቁን ነው ያብራራችው።

በመሆኑም ከከተራ ጀምሮ ባሉ ሥነ ስርዓቶች ሁሉ አምስት ሺህ በጎ ፈቃድ ወጣቶችን በየታቦት ማደሪያዎች ይሰማራሉ ማለቷን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review