በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ያመዝናል- ኢንስቲትዩቱ

AMN – ህዳር 3/2017 ዓ.ም

በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚያመዝን መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅ፣ ምሥራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡብ አከባቢዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ቀጣይነት እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ከኦሮሚያ ክልል ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ወላይታ፣ ኮንሶ፣ ጌዲኦ፣ ባስኬቶ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፤ አሌ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እንዲሁ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንታ፣ ከፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳዉሮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፤ ከሱማሌ ክልል ዳዋ፣ ሊበን፣ አፍዴር፣ ሸበል፣ ኖጎብ፣ ቆራሂ፣ ዶሎ ፋፋን፣ ኤረር እና ጃረር፤ እንዲሁም ሀረሪ እና ድሬዳዋ ዞኖች ላይ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም ከክረምት ጀምሮ ዝናብ እያገኙ ባሉት አከባቢዎች ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፤ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ የኢታንግ ልዩ ዞን፣ ኑዌር አኝዋክ እና ማዥንግ ዞኖች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት በተለይም ከሳምንቱ አጋማሽ በኋላ አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ከአማራ ክልል በምዕራብ፤ ሰሜን፣ ማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር፤ ምስራቅ፤ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም፤ አዊ ዞኖች እና ባህርዳር ዙሪያ፤ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋህግምራ፤ ሰሜን ሸዋ፣ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን፤ ከትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለዉ ዝናብ ሊኖር ይችላል ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ የምዕራብ፣ የደቡብና የደቡብ ምስራቅ ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ፋንቲ፤ ማሂ፣ ሃሪ፣ እና ጋቢ ዞኖች፤ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)፤ አዲስ አበባ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች በተለይም በጥቂት ቀናቶች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለዉ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ስለሆነም በሚኖሩት ደረቅ ቀናቶች የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review