በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ከሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች ውስጥ 56 በመቶ የሚሆኑት በተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሚዘዋወሩ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ ያለውን የጥላቻ ንግገር እና ሐሰተኛ መረጃ ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ጥናት አካሂዷል።
በጥናቱ መሰረትም በሀገሪቱ የሚታየው የሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ታምራት ደጄኔ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከ44 ሚሊየን በላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ያስታወቁት የዋና ዳይሬክተሩ አማካሪ፣ ከነዚህም መካከል 4 ሚሊየን የሚሆኑ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ምንም እንኳን ከአጠቃላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር አንፃር ሲታይ አነስተኛ ቢሆንም፣ አጀንዳ ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አስታውቀዋል።
በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩት ሐሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች በአብዛኛው በፅሁፍ እና በተንቀሳቃሽ ምስሎች የሚሰራጩ መሆኑንና፣ 56 በመቶ የሚሆኑት የሚተላለፉት በታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች አማካኝነት መሆኑንም ጥናቱ አመላክቷል።
በፖለቲካ አመለካከት፣ በብሔርና በሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩት ሐሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች፣ በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዳይኖር ዜጎችን ለአመፅና ለግጭት የማነሳሳት እንዲሁም ህዝብና መንግስት ተረጋግተው ሥራቸውን እንዳይሰሩ የማድረግ ዓላማ ያላቸው ናቸውም ተብሏል።
የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች አቅም ግንባታ ስራ እንዲሰሩና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ እንዲከፍቱ ማድረግ፣ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ሪጉሌሽን ፖሊሲ ማውጣትና ኩባንያዎቹ ከሚያገኙት ገቢ በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ህግ መሰረት እንዲከፍሉ ማድረግ በጥናቱ መሰረት በመፍትሔነት የተቀመጡ ሀሳቦች ሆነዋል።
በደሳለኝ መሐመድ እና በየሺዋስ ዋለ