የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮምሽነር ዶ/ር ዘለቀ ተመስገን የቻይና ሕዝብ የፖለቲካ ምክክር ጉባኤ ብሔራዊ ኮሚቴ ምክትል ሊቀ መንበር እና የቻይና የኢንዱስትሪና የንግድ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ጋኦ ዩንሎንግ እና የልዑክ ቡድናቸውን አነጋግረዋል፡፡
ዶክተር ዘለቀ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ቻይናውያን ባለሀብቶች ቀዳሚ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ ከ3 ሺህ 500 በላይ ቻይናውያን 9.5 ቢለየን ዶላር ፈሰስ በማድረግ በኢንቨስትመንት እንደተሰማሩ ተናግረዋል፡፡
ይህንን በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚ ልማት እና የንግድ ትብብርን ይበልጥ ለማጠናከርም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር ከባለድርሻ አካለት ጋር በተለየ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡
በመጪው ግንቦት 4 እና 5/2017 በሚደረገው የኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ ፎረም ላይ ቻይናውያን እንዲሳተፉ ኮሚሽነር ዘለቀ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጋኦ ዩንሎንግ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የልማት እንቅስቃሴ አድንቀው በቻይና በተለያየ ደረጃ ያሉ ከ55ሺ በላይ የንግድ ማህበራት በኢትዮጵያ መጥተው መዋለንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡
የቻይና መንግስትም ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚ ልማት እና የንግድ ትብብርን ይበልጥ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለውም ጋኦ ዩንሎንግ ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም ልኡክ ቡድኑ በተለያየ ዘርፍ ከተሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጉን ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡





All reactions:
1212