በማይናማር በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾች ቁጥር 1 ሺህ 7 መድረሱን እና ወደ 2 ሺህ 389 የሚሆኑት የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው እንዲሁም 30 የሚሆኑት የደረሱበት አለመታወቁን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
የንብስ አድን ሰራተኞችም በፍርስራሽ ሥር የሚገኙ በህይወት ያሉ ሰዎችን ለማትረፍ ርብርብ እያደረጉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በትናንትው እለት በሬከረተር ስኬል 7.7 በተመዘገበ ርዕደ መሬት የተመታችው ማይናማር፣ እስከ ዛሬ የዘለቀ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዷ ተገልጿል፡፡
ርዕደ መሬቱ በታይላንድ ባንኮክ በፈጠረው ንዝረትም ህንፃዎች የተደረመሱ ሲሆን፣ 15 ሰዎች በፍርስራሽ ሥር መታፈናቸውን እና 100 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁ ተነግሯል፡፡
በአደጋው የማይናማር ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ በሆነችው ማንዳላይ ከ1 ሺህ 500 በላይ ቤቶች መውደማቸው መገለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።
በማይናማር እና በታይላንድ ጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የነብስ አድን ድጋፎች እና እርዳታዎች እየተደረጉ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ