በሟች ወ/ሮ ቀነኒ አዱኛ ዋቆ አሟሟት ዙሪያ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

You are currently viewing በሟች ወ/ሮ ቀነኒ አዱኛ ዋቆ አሟሟት ዙሪያ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም

በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሰንሻይን ቤቶች ፊት ለፊት ከሚገኘው ውዳሴ ህንፃ ላይ ነዋሪ የነበረችው ሟች ወ/ሮ ቀነኒ አዱኛ ዋቆ መጋቢት 01 ቀን 2017 ዓ/ም ከሌሊቱ 10፡00 ሠዓት አካባቢ ከቤቷ የማብሰያ ክፍል በኩል ካለው በረንዳ 5ኛ ፎቅ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ወድቃ ለህክምና እርዳታ ወደ ያኔት ሆስፒታል እየተወሰደች ባለበት ወቅት ህይወቷ ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃው ከደረሰው በኋላ የምርመራ ቡድን በማዋቀርና ቦታው ድረስ በመሄድ ተገቢውን የቴክኒክና የታክቲክ መረጃዎችን ያሰባሰበ መሆኑን የገለጸ ሲሆን የሟችንም አስከሬን ወደ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ለተጨማሪ ለምርመራ እንዲሄድ አድርጓል፡፡

ሟች ወ/ሮ ቀነኒ አዱኛ በወቅቱ ከበረንዳ ላይ በወደቀችበት ሰዓት ፖሊስ በቤቱ ውስጥ የነበረውን ባለቤቷን ድምፃዊ አንዷለም ጎሳን በቁጥጥር ስር በማዋልም ምርመራ እያጣራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቀጣይ የመጨረሻውን የምርመራ ውጤትም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ከፖሊስ የወንጀል ምርመራ ውጤት በፊት የሚናፈሱ መረጃዎች ተገቢነት የሌላቸው መሆኑን የገለጸው ፖሊስ በምርምራ ሒደቱ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅህኖ በመገንዘብ የተሳሳተ መረጃ የሚያስተላልፉ እና የሚያሰራጩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review