በሪፎሙ በወንጀል መከላከልም ሆነ በወንጀል ምርመራ ብቁ ሆኖ ለመገኘት ትልልቅ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተን አስደናቂ ውጤቶችን አስመዝግበናል ሲሉ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ ገለፁ።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ የፌደራል፣ የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፖሊስ ኮሚሽነሮች መደበኛ ጉበዔን መክፈታቸውን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ ፣ 19ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ ሀገርን በጋራ ለማፅናት እና የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ በተፈረመው መሠረት በቀጣይ በቅንጅትና በመደጋገፍ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሰብአዊ መብት አያያዝን በማጠናከር ሀገራዊ ራዕይን ለማሳካት ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም ሌሎች ሕጎችን በማክበርና በማስከበር ሕብረተሰቡን በወንጀል መከላከልና ምርመራ በማሳተፍ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት እየጠበቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በጉባኤው ማንኛውም የወንጀል ተጠርጣሪ የትኛውም ክልል ተደብቆ ማምለጥ በማይችልበት ሁኔታ ላይ በመወያየት እና በአፈፃፀሙ ላይ ስምምነት ላይ በመድረስ ኢትዮጵያ የጀመረችው የኢኮኖሚ ሪፎርም ግቡን እንዲመታ የፀጥታ ዘርፉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በወንጀል መከላከልም ሆነ በወንጀል ምርመራ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይኖርብናል ብለዋል።
በባለፉት ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች ሲስተዋሉ የነበሩ ወንጀሎች ላይ ለተመዘገበው ውጤት የፌደራልና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፀጥታና የደኅንነት አካላት፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላት እንዲሁም ከፖሊስ ጎን ተሰልፎ የዜግነት ኃላፊነቱን እየተወጣ ለሚገኘው ኅብረተሰብ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ ምስጋና አቅርበዋል።