የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለፉት ወራት ባከናወናቸው የራስ ገዝነት የሪፎረም ጉዞዎች ዉጤታማ ተግባራትን ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
የዩኒቨርስቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶክተር) የራስገዝነት የሪፎርም አፈጻጸምና የዩኒቨርስቲውን 75ኛ አልማዝ ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክተዉ መግለጫ ሰጥተዋል።
ባለፉት አመታት እንደ ሀገር በትምህርት ስርዓቱ ላይ አጋጥሞ የነበረዉን የጥራት ስብራት ለመቅረፍ አዲስ የትምህርት ፖሊሲና የአሰራር ስርዓቶች ተዘርግተዉ ወደ ስራ መግባታቸው፣ አሁን ላይ በመማር ማስተማሩ ላይ ጥሩ ውጤቶች መታየታቸውን ዶክተር ክፍሌ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በሪፎርም ስርዓት ዉስጥ የመጀመሪያዉ ራስ ገዝ ሆኖ እንዲወጣ መደረጉ፣ በትምህርት ስርዓት ዉስጥ የተሸለ ለዉጥ እንዲመጣ ከማድረግ ባሻገር፣ የበቃ እና ኢንዱስትሪው የሚፈልገዉን የተማረ የሰው ሀይል እያፈራ መሆኑም በመግለጫዉ ተነስቷል።
ዩኒቨርስቲዉ በ2016 ዓ.ም ወደ ራስገዝነት የሚደረገዉን ሽግግር እንዲያግዝ ወደ ስራ ያስገባው የአመራር ቡድን፣ አሁን ላይ ጠንካራ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ዶክተር ሳሙኤል ጠቁመዋል።
ቡድኑ የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣ የተለያዩ ተግባራትን እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
አስተዳደራዊ ነጻነትን የተጎናጸፈው ዩኒቨርስቲዉ፣ በአለም አቀፈፍ ደረጃ ሀገርን የሚጥቅሙ ምርምሮችን እና ዉይይቶችን እያከነወነ ይገኛልም ተብሏል።
እስካሁን ከ280 ሺ በላይ የሰለጠነ የሰዉ ሀይልን ማፍራት የቻለዉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የ75ኛ የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን በልዩ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቁንም አመላክተዋል፡፡
በሩዝሊን መሀመድ